በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት

“ምግብ ለመግዛት ከቤቱ የወጣ የንግድ ባንክ ሠራተኛ በኤርትራ ወታደሮች ተገድሏል፤ አስከሬኑ አስፋልት ላይ አድሮ በማግሥቱ ታንክ ግማሽ አካሉን ጨፍልቆታል” የዓይን ምስክሮች

ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 24, 2021)፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የተፈጸመውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ።

ኮሚሽኑ ባወጣው በዚህ ሪፖርት፤ በአክሱም የተፈጸመውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ከአንድ መቶ በላይ የሞቱ እና ሌሎችም ብዛት ያላቸው የተጎጂ መረጃዎችን የሰበሰበ መኾኑን አስታውቋል።

አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አክሱም ቅርንጫፍ ሠራተኛ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከረፋዱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ምግብ ለመግዛት ከቤቱ ሲወጣ “አብነት ሆቴል ፊት ለፊት ሲደርስ የኤርትራ ወታደሮች መጀመሪያ እግሩ ላይ ቀጥሎ ደረቱ ላይ በጥይት መተው እንደገደሉት” በርካታ ነዋሪዎች እንደመሰከሩ ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ ገልጿል። አክሎም ይኸው ሟች ሳይቀበር አስፋልት ላይ እስከማግሥቱ ኅዳር 20 ቀን ድረስ መቆየቱንና ታንክ እሬሳው ላይ ስለሔደበት “ከወገቡ በታች ተጨፍልቆ እጁና እግሩ ተቆራርጠው እንደነበር” የአስከሬኑን ሁኔታ ያዩ የዓይን ምስክር መግለጻቸውን ኢሰመኮ ሪፖርት አድርጓል።

ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ከአክሱም ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኝና ሓፀቦ(ሞረር) በተሰኘች ቦታ ላይ 10 ሰዎች በወታደራዊ የአየር ጥቃት መጎዳታቸውን፤ ከእነሱም ውስጥ አምስቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ፤ አንድ ቄስ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ከነዋሪዎች እና ከሕክምና ባለሞያዎች መረዳቱን ኢሰመኮ በሪፖርቱ ገልጿል።

13 ገጾች ያሉት ይህ ሪፖርት፤ በመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ተገኙ ያላቸውን መረጃዎች ያካተተ ዝርዝር ጉዳዮችንም የያዘ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን ቀንጭበን እንደወረደ እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። የሪፖርቱን ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)

በጦርነቱ ሁኔታ በሲቪሎች የደረሰው ጉዳት (ኅዳር 9 ቀን እስከ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.)

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ፤ በቀድሞው የክልሉ መንግሥት ሥር የአክሱም ከተማን ሲያስተዳድር የነበረው የአካባቢው መስተዳድር አካል ከኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከተማዋን ለቅቆ መውጣት ጀመረ። በዕለቱ በአክሱም ከተማ እና ከከተማው በቅርብ ርቀት በነበሩ ቦታዎች ላይ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምፅ ይሰማ የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ አካባቢዎች በወታደራዊ የአየር ጥቃት ጭምር ሲናወጡ እንደነበር ነዋሪዎች ያስረዳሉ። የከባድ መሣሪያና የተኩስ ድምፁ እስከ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የዘለቀ ነበር።

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት
በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት

በዚህ ምክንያት “የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም ከሽረ እና ከሌሎች አካባቢዎች ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ሰዎች በድንጋጤ ተውጠው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሸሹ።” ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የነበረው “የከባድ መሳሪያ ተኩስ እና የወታደራዊ አየር ጥቃቱ” በሲቪል ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ሓፀቦ(ሞረር) ከአክሱም ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ቦታ 10 ሰዎች በወታደራዊ የአየር ጥቃቱ የተጎዱ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ፣ አምስቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ፤ አንድ ቄስ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ነዋሪዎች እና ተጎጂዎቹ የሕክምና እርዳታ ያገኙባቸው ሆስፒታል ባለሞያዎች ያስረዳሉ። “የሞቱት አምስት ሰዎች የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ማንነታችውን ለመለየት ሳይቻል ተቀብረዋል።” በተመሳሳይ ቀን በአክሱም ከተማ ዳሞ ሆቴል በመባል በሚታወቀው አካባቢ ወ/ሮ ወይናረግ ረዳ የተባሉና በአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚታወቁ እናት መኖሪያ ቤት በከባድ መሳሪያ ተመቶ፣ እሳቸውና እና ሦስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ሞተዋል።

በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት
በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት

እጃቸው፣ እግራቸው እና ሌሎች የሰውነት ክፍላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ አክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል እና አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰዱ ሰዎች በርካታ ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች ለኢሰመኮ እንደገለጹት በኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ቅድስት ማርያም ሆስፒታል ጉዳት ደርሶባቸው ከመጡ ሰዎች መካከል አስሩ ሞተዋል። ከእነዚህ መካከል “አንድ ከ70 ዓመት በላይ እንደሚኾናቸው የሚገመቱ እናት አፋቸው እና መንጋጋቸው ሙሉ በሙሉ በመገንጠሉ አሰቃቂና ሕክምና ለመስጠት አስቸጋሪ እንደነበርና ለተሰወኑ ቀናት ምግብ በሕክምና ቱቦ እየተሰጣቸው ከቆዩ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን” የሕክምና ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የተጎጂዋን ሁኔታ የሚያሳይ የምስል ማስረጃ ተመልክቷል።

… የቅድስት ማርያም ሆስፒታል ሠራተኞች ሲያስረዱ፣ “ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የኤርትራ ወታደሮች ወደ ሆስፒታሉ ገቡ። ከሆስፒታሉ ፋርማሲ መድሃኒት እና የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች ዘርፈው የማይፈልጉትን ደግሞ አወደሙ። በድንገተኛ ክፍል የነበረ አንድ ታካሚ በተኛበት ተኩሰው ገድለው እና የሆስፒታሉን መኪና ይዘው ሔዱ። የኤርትራ ወታደሮች የሆስፒታሉን ሠራተኞች አፀያፊ እና የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረጉ ስድቦች ይሳደቡ ነበር።” አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል በተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት እና የኤርትራ ወታደሮች በተለያየ ወቅት አራት ጊዜ እንደተዘረፈ፤ እንዲሁም በሆስፒታሉ የኮረና ማዕከል ኾኖ ሲያገለግል በነበረ ሕንፃ በከፍተኛ ወጪ የተገዙ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎች፣ የታማሚ አልጋዎች እና ፍራሾች ሳይቀር በኤርትራ ወታደሮች እንደተዘረፉ የዓይን እማኞች ይናገራሉ። ማዕከሉ የደረሰበትን ጉዳት የሚያሳይ የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ ለኮሚሽኑ ሰጥተዋል።

በሲቪል ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት

በአክሱም ከተማ በሲቪል ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ኮሚሽኑ ወደተወሰኑት አካባቢዎች በመዘዋወር ተመልክቷል። ለምሳሌ ብራና ሆቴል በተባለ የግለሰብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። የሆቴሉ ባለቤቶች እንደሚሉት “መከላከያ ሠራዊቱ ከብራና ሆቴል በቅርብ ርቀት የሚገኝ የአንድ የሕወሓት ጄኔራል ሆቴል ለመምታት አስበው፤ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ከሕወሓቱ ጄኔራል ምንም ንክኪ የሌለውን ብራና ሆቴልን መትተዋል”። በጥይት የሆቴሉን የውጭ መስተዋቶች ሙሉ በሙሉ ሲያወድሙ፤ ወደ ውስጥ በመዝለቅም አብዛኛውን የሆቴሉን ንብረቶች ከጥቅም ውጪ እንዲኾን አድርገውታል ብለዋል። ኮሚሽኑ ምርመራውን እስካካሔደበት ቀን ድረስ ሆቴሉ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመረ ተመልክቷል። የሆቴሉ ባለቤቶች “ሆቴሉ በሚያሳዝን ሁኔታ እንደተመታ” የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከአካባቢው ጊዜያዊ መስተዳድር አካላት የደረሳቸው ሲሆን፤ ደበዳቤውና የደረሰውን ጉዳት የሚያመላክቱ የምስል ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ አሳይተዋል።

ብራና ሆቴል
በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት

የኤርትራ ወታደሮች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሱት ጥቃት (ኅዳር 16 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም.)

ኢትየጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ከከተማዋ ሲወጡ እንደታዩ፤ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. አክሱም ላይ “ምንም የወታደር እንቅስቃሴ” በከተማዋ እንዳልነበረ የከተማው ነዋሪዎች ለኢሰመኮ አስረድተዋል። ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ግን “ብዛት ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች በከተማዋ መታየት ጀመሩ። በሦስት የተለያዩ የከተማዋ ቦታዎች ማለትም በማይ ኩሖ፣ በሳሙና ፋብሪካ እና ፅልዓ በተባሉ ቦታዎች ሰፈሩ። ከኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ ከፍተኛ የኾነ የተኩስ ድምፅ በከተማዋ መሰማት ጀመረ።”

ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች ተኩሱ ስለተጀመረበት ምክንያት እንዳማያውቁ ይናገራሉ። የተወሰኑ ሰዎች ግን ስለ ሁኔታው የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ። አንዳንዱ “ተኩሱ የተነሳው የታጠቁ የአካባቢው ሚሊሻዎች በኤርትራ ወታደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው ስለነበር፤ በዚህ የተቆጡት የኤርትራ ወታደሮች ሲቪል ሰዎችን መግደል” መጀመራቸውን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ “የኤርትራ ወታደሮቹ የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን ለመዝረፍ ስለፈለጉ እና የአካባቢው ሰውም ይህንን ስለተቃወመ ሲቪል ሰዎችን መግደል ጀመሩ” ይላሉ። ሌሎች የኮሚሽኑ መረጃ ምንጮች ደግሞ በአካባቢው የነበሩ ሚሊሻዎች ከተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመኾን በኤርትራ ወታደሮች ላይ በሰነዘሩት ጥቃትና የኤርትራ ወታደሮች በአጸፋ በሰነዘሩት የበቀል እርምጃ በሲቪል ሰዎች ላይ በተለይም በአብዛኛው በወንዶች ላይ ያነጣጠረ ግድያና ጉዳት አደረሱ በማለት ይገልጻሉ።

… አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አክሱም ቅርንጫፍ ሠራተኛ እንደነበረ የተረጋገጠ ሰው (ስሙ በኮሚሽኑ የሚገኝ) ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ሙሉ ቀን ቤቱ ቆይቶ ከረፋዱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ምግብ ለመግዛት ወጥቶ “አብነት ሆቴል ፊት ለፊት ሲደርስ የኤርትራ ወታደሮች መጀመሪያ እግሩ ላይ ቀጥሎ ደረቱ ላይ በጥይት መተው እንደገደሉት” በርካታ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ሟች ሳይቀበር አስፋልት ላይ እስከ ኅዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. መቆየቱንና ታንክ እሬሳው ላይ ስለሔደበት “ከወገቡ በታች ተጨፍልቆ እጁና እግሩ ተቆራርጠው እንደነበር” የአስከሬኑን ሁኔታ ያዩ የዓይን ምስክር ገልጸዋል።

የተጎጂ ቤተሰቦችና የዓይን ምስክሮች ለኢሰመኮ እንዳስረዱት “ሙሉብርሃን ገብረመድህን(ወዲ ጎንየ)የተባለ የ38 ዓመት ሰው እርጉዝ ሚስቱ እና ልጆቹ ፊት እንዲሁም መኮንን ጠሚዓ የተባለ ሰው በልጆቹ ፊት ተገድለዋል፣ ጉዕሽ መኮንን የተባለ የ38 ዓመት የእንስሳት ሐኪም ልጁ እያለቀሰ ከቤት አውጥተው ገድለውታል፣ ቢትወደድ ታደሰ ከበደ የተባለ የ51 ዓመት ሰው በጥይት የተገደሉ ሰዎች ሬሳ ለማንሳት ሲሞክር ጉሮሮው እና ደረቱ ላይ ተመቶ ቤተሰቡን ለማሳወቅ ባለመቻሉ በአካባቢው ሰዎች ተቀብሯል። ሙሉጌታ ጥዓመ (ወዲ ውቅሮ)የተባለ ወጣት ኅዳር 20 ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ የተገደሉት ሰዎች ለማንሳት ሲሞክር በሦስት ጥይት ተመቶ ሞቷል።”

ሙሉጌታ ፍስሃ የተባለ ዕድሜው በግምት 14 ዓመት የሚኾን ልጅ እናቱ ወ/ሮ ተጫዊት በኤርትራ ወታደሮች ተገድለው እያለቀሰ ወደ ወደቁበት ቦታ እየሮጠ ሲሔድ እሱንም ጨምረው እንደገደሉት የሟቾች የቅርብ ቤተሰብ ያስረዳሉ። “ኤፍሬም ዓለም የተባለ ወጣት የልጁ ክርስትና ቀን በመኾኑ ከጓደኞቹ ጋር ወደ ቤት እየሔደ እያለ እሱን እና ሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ተገድለው ከመካከላቸው አንዱ ብቻ ተርፏል። በሪሁ ገብረ ሩፋኤል የተባለ ወጣት የልጁ የአንድ ዓመት ልደት እያከበረ እያለ ከቤት አውጥተው ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር አንድ ላይ ገድለውታል።”

በኤርትራ ወታደሮች በጥይት የደበደቡት በአክሱም የሚገኝ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን
በኤርትራ ወታደሮች በጥይት የደበደቡት በአክሱም የሚገኝ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን

… በሲቪል ሰዎች ላይ ከደረሰው የሞት እና የአካል ጉዳት በተጨማሪ የሃይማኖት ተቋማትና የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች የንብረት ጉዳቶች ደርሰዋል። ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ገደማ እስከ ረፋዱ 11፡00 ሰዓት ቁጥራቸው ያልታወቁ የኤርትራ ወታደሮች በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለው የመቃብር አከባቢ ኾነው የቤተ ክርስቲያኑን ሕንፃ ለማፍረስ በትግርኛ “ህረሞ ... ህረሞ …" (በለው … በለው …)እያሉ በጥይት ሲደበድቡት እንደዋሉ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ የዓይን እማኞች ለኮሚሽኑ ገልጸዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ