በአጣየ አካባቢ ኦነግ ሸኔ በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ ግድያ መፈጸሙ ተነገረ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ የአጣዬ ከተማ
በጥቃቱ በርካቶች ተገድለዋል፤ መከላከያ እና የአማራ ልዩ ኃይል ወደ አካባቢው ተጉዘዋል
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 20, 2021)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ በአጣየ እና አካባቢው ከትናንት ምሽት ጀምሮ የኦነግ ሸኔ ቡድን ጥቃት በማድረስ ላይ ስለመኾኑና በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ እየተካሔደ መኾኑ እየተሰማ ነው።
ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች ተንቀሳቅሶ ወደ አጣየ አካባቢ ገብተው ጥቃት የሰነዘሩትን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ለመከላከል የአማራ ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ኃይል ወደ አካባቢው ገብተዋል ተብሏል።
የአካባቢውን ነዋሪዎች በመጥቀስ እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በምሽት ሰርጎ ገብቶ ጥቃት የፈጸመው የኦነግ ሸኔ ቡድን፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ነው ተብሏል።
ከትናንት ምሽት ጀምሮ የኦነግ ሸኔ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት በርካታ ሰዎችን የገደሉ ሲሆን፤ ዘረፋም አካሒደዋል። ለጊዜው ግድያ የተፈጸመባቸው ግለሰቦች ቁጥር ይፋ ያልተደረገ ሲሆን፤ ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች በባንክ ቤቶች ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን የሚጠቁሙ ናቸው። በአካባቢው ታዋቂ የኾኑ ግለሰቦች ግድያ እንደተፈጸመባቸውም እየተነገረ ነው።
ከመከላከያ እና ከአማራ ልዩ ኃይል ሌላ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን በመከላከል ላይ ስለመኾናቸው እየተነገረ ነው።
በአጣየ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ፤ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ወጣቶች የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)