PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ወደተኩስ አቁሙ የተገባበትን ምክንያቶች ገልጸዋል

ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 30, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ተኩስ አቁም ዙሪያ ትናንት ምሽት ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ተሰማ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ መቶ በላይ ጋዜጠኞች በተገኙበት ያደረጉት ማብራሪያ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች የነበሩበት እንደነበር ታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ ንግግር የሚከተለው ሲሆን፤ ለመመልከትና ለማድመጥ የማጫወቻውን ቁልፍ ይጫኑ!

በዚሁ ጉዳይ ላይ የትግራይ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ያቀረበው አጭር ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፤ ጽሕፈት ቤቱ በመረጃ ገጹ ያሰፈረው ሙሉ ሪፖርት የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

“የታክቲክ ለውጥ አድርገናል” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ

ዛሬ ማምሻውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሚዲያ ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው ነበር። የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በምርጫው ወቅት ሚዲያዎች በነበራቸው አስተዋጽኦ ዙሪያ ምስጋና ባቀረቡበት ንግግራቸው ስለ ትግራይ ተኩስ አቁም ዙርያ ሰፊ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ጠ/ሚ ዐቢይ ሲናገሩ እስካሁን ለእርዳታ ብቻ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ ኾኗል። ይህም ለክልሉ ፌደራል መንግሥት ሊሰጠው ከሚችለው ዓመታዊ በጀት 10 እጥፍ በላይ ነው። በተረጅዎች አማካኝነት እርዳታው ለጁንታው እንዲደርሰው ይደረግ ነበር፤ ሁለት ልጅ ያለው 5 ና 7 እያለ በተረጂዎቹ አማካኝነት ጁንታው እርዳታውን ያገኝ ነበር። ይህም ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ ከውስጥም ከውጭም ያሉ አካላት ማናቸውም እየተደረገ ላለው ድጋፍ እውቅና መስጠት የፈለገ የለም::

መንግሥት ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ እየሠራ የነበረ ቢኾንም በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ከውስጥ የሚደርሱበት ጫናዎች እና በመንግሥት ላይ ከውጭ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች የሚከፈለው ዋጋ ለማን ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርገዋል። ምንም አቅም የሌለው ቀሪ የጁንታው አካል አዲሱ ታክቲክ እኛን አመድ እንዳደረጉን በተራዘመ ጦርነት አገሪቱም አብራ እንድትዳከም እና እንድትወድቅ ማድረግ ነው የሚል ነው።

እኛም ይህን በመረዳት እየሞተ ካለ ቡድን ጋር አብሮ ላለመሞት የታክቲክ ለውጥ ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ሳምንት ተወያይተን የወሰነውም መከላከያው ደጀን ወደሚያገኝበት አካባቢ እንዲመጣ ሕዝቡም ከስሕትቱ የሚማርበት የጥሞና ጊዜ መስጠት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም እውነታውን የሚረዳበት ሁኔታን መፍጠር አለብን በሚል ነው የተወሰነው።

ጦሩ ትግራይን ለቅቆ እንዲወጣ ከወሰኑ በኋላ ትናንት እስከ እኩለ ሌሊት ከብዙ የዓለም መሪዎች የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው በተለይም ጦሩን ሲከስሱ እና ሲወቅሱ የነበሩ አገራት በጦሩ መውጣት መበሳጨታቸውን ተናግረዋል።

ለሚዲያ ፍጆታ የማይውለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ብዙ አስገራሚ አሳዛኝ እና ለሕዝቦች አብሮነት ሲባል በትዕግሥት የታለፉ አናዳጅ አዳዲስ መረጃዎች የተሰሙበት ነበር። በዚህ ሁሉ ገለጻ ውስጥ ግን ሁሉም ያደነቀው እና የኮራበት ነገር የመከላከያ ሠራዊቱ ጀግንነት፣ ትዕግሥት እና ያለፈባቸውን ፈታኝ ሁኔታዎችን ነው::

አንዳንዶች ተሸንፈው ነው ይላሉ 80 በመቶ ወታደራዊ ትጥቅ ከመንግሥታዊ ሥልጣን ጋር የያዙ አካላትን በሦስት ሳምንት አሽንፈን አሁን ማንም በሌለበት እንዴት ተሸንፈን እንወጣለን ሰው ይህን ማገናዘብ ይኖርበታል ብለዋል። በክልሉ ብሎም በመቀሌ የነበሩ ዋና ዋና የምንፈልጋቸውን ነገሮች አውጥተናል አሁን መቀሌ ምንም ዐይነት የስበት ማዕከል አይደለችም፤ ምንም ለወታደራዊ ስትራቴጂነት የቀራት ነገር የለም ብለዋል።

እስከ ቅርብ ሰዓት ድረስ ማንም የሕወሓት አመራር ወደ ከተማዋ እንዳልገባም አረጋግጠናል ብለዋል የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፖርክ በተዘጋጀውና ከ100 በላይ ጋዜጠኞችና ከ600 በላይ ታዳሚዎች በትገኙበት ሥነሥርዓት ላይ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ