የአማራ ብልጽግና ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጠ
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ
ፓርቲው እስከዛሬ ካወጣቸው መግለጫዎች ውስጥ እጅግ ጠንካራ ነው
ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 29, 2021)፦ የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መሥዋእትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መኾናቸውን እናሳውቃለን ሲል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ። ፓርቲው እስከዛሬ ካወጣቸው መግለጫዎች ውስጥ እጅግ ጠንካራ ነው።
ፓርቲው “የአማራ ሕዝብ በሽብርተኞች ሒሳብ እንዳይወራረድበት አይፈቅድም” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫው ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌላ መኾኑን ደግመን እናስታውቃለን ብሏል። የፓርቲው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
"የአማራ ሕዝብ በሽብርተኞች ሒሳብ እንዲወራረድበት አይፈቅድም" የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
የአሸባሪው ትሕነግ (ሕወሓት) አመራሮች በተደጋጋሚ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት የአማራን "ኤሊት" ተጠያቂ በማድረግ ሒሳብ እንደሚያወራርዱ ነግረውናል። ትሕነጎች የሚያወራርዱትን ሒሳብ "ከአማራ ልሂቃን" ጋር ያያይዙት እንጂ፤ እውነታው ግን የአማራን ሕዝብ ስለማለታቸው ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለንም። ለዚህ ተጨባጭ ግምገማ አስረጅ ምሳሌው ትሕነግ በታሪካዊ ጠላትነት የፈረጀው የአማራን ሕዝብ እንደአጠቃላይ እንጂ የአማራን ልሂቃን በለዬ ሁኔታ አይደለም። ስለኾነም የትሕነጎች ሒሳብ ማወራረጃ የአማራ ሕዝብ እንጂ ልሂቁ ብቻ አይደለም። ይህ አዲሱ ማደናገሪያቸው ነው። ጥላቻቸው በአማራ ሕዝብ ላይ ነው። ስሁት ትርክት የፈጠሩት፣ ለዚህ ማስፈጸሚያ መዋቅር የነበሩት ልሂቁን ብቻ ሳይኾን አማራን እንደሕዝብ ለመጉዳት ኾነ ብለው አስበው፣ አቅደውና አጥንተው ነው። ጥላቻው የአማራ አርሶ አደር ጓዳ ድረስ የዘለቀ ነው።
በተግባር ፈጽሞ የማይሳካ ቢኾንም፤ በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ዛሬ "ሒሳብ እናወራርዳለን" ሲሉ ቢሳካላቸው የአማራ አርሶ አደር ጓዳ ድረስ የዘለቀ የሰይፍ በትር የመዘርጋት ሰይጣናዊ ተነሳሽነት አላቸው።
በትሕነግ የሒሳብ ማወራረድ እሳቤ የሚዘረፈው ንብረት የአማራ ሕዝብ ንብረት ሲሆን፤ ሊደፈሩ የታሰበው ደግሞ የአማራ እናትና እኅት ናቸው። ተገዳዩ ደግሞ ሁሉም አማራ ነው።
ይሁንና ዛሬ መላው የአማራ ሕዝብ በትሕነግ ዳግም ሊሰነዘርበት የታሰበውን የጥፋት ሰይፍ በደንብ ተረድቶታል። የብሔራዊ ንቃት ስሜቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል። የሞራል ልዕልና ከፍታውን ባለበት አስጠብቋል። በፍቅር ለመጣ በተለመደ ሰብአዊ ጀግንነቱ እጁን ይዘረጋል፤ በጥላቻ ለሚመጣ ተገቢውንና የማያዳግም ትምህርት ሰጥቶ ይመልሳል።
የአማራ ሕዝብ የትኛውንም በቀል ለመበቀል ፍጹም አልተዘጋጀም። ይህ ማለት ግን "ሒሳብ እናወራርዳለን" ባዮችን በዝምታ ይታገሳል ማለት አይደለም። ከዳተኛና ፀረ-ሕዝብ የኾኑ የትኞቹንም ጠላቶቹን ያለ ምህረት ይታገላል።
ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መሥዋዕትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መኾናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን።
እነዚህን አካባቢዎች ደግሞ ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ፣ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌለ መኾኑን ደግመን ደጋግመን እናረጋግጥላችኋለን።



