ኢድና ሞል በ810 ሚሊዮን በጨረታ ተሸጠ

ኢድና ሞል
በባንክ እዳ የቀረበውን ሕንጻ ጨረታ ያሸነፈው የቻይና ኩባንያ ነው
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 7, 2021)፦ “ኢድና ሞል” በመባል የሚታወቀው እና በተክለብርሃን አምባዬ ባለቤትነት የተያዘው ሕንጻ ባለበት የባንክ እዳ፤ ለጨረታ ቀርቦ አንድ የቻይና ኩባንያ 810 ሚሊዮን ብር ዋጋ ሰጥቶ አሸናፊ ስለመኾኑ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
አቶ ተክለብርሃን አምባዬ በስማቸው ባቋቋሙትና “ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማኅበር” ተብሎ ለሚጠራው የኮንስትራክሽን ድርጅታቸው “ኢድና ሞል”ን በመያዣነት ተጠቅመው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ ባለመክፈላቸው፤ ባንኩ ኢድና ሞልን በሐራጅ ለመሸጥ ጨረታ አውጥቶ ነበር።
ባንኩ ባወጣው በዚሁ ጨረታ ላይ የመነሻ ዋጋ ብሎ አስቀምጦ የነበረው 236.9 (ሁለት መቶ ሠላሳ ስድስት ነጥብ ዘጠኝ) ሚሊዮን ብር ነበር።
በ1938 ካሬ ሜት ላይ ያረፈው ኢድና ሞል የሚገኘው በቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ ሲሆን፣ ባንኩ የሸጠው ሙሉውን ሕንጻ ከነ ሲኒማ ቤቶቹ፣ የሲኒማ ማሳያ መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች፣ የመዝናኛና መጫወቻ ቁሳቁሶቹ ጋር መኾኑን ለመረዳት ችለናል። (ኢዛ)