የጋምቤላ ጥቃትና ታፍነው የተወሰዱት ሕጻናት ጉዳይ

Gambela
የሙርሊ ታጣቂዎች ወደ 13 የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል፤ 21 የሚሆኑ ሕጻናት ታፍነው በሞርሊ ተወስደዋል

(ዶቼቬለ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን በጎን እና በጆር ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሣ ታጣቂዎች በጣሉት ጥቃት ከአስራ ስምንት ሰዎች በላይ መገደላቸውንና ከ22 በላይ ሕጻናት ታግተው መወሰዳቸውን ተቀማጭነቱን ለንደን ላይ ያደረገው ”አኝዋ ሰርቫይቫል” የተሰኘው ድርጅት ገለፀ።

መንግሥት ርምጃ አልወሰደም

”አኝዋ ሰርቫይቫል” የተሰኘው የጋምቤላ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መንግሥት ምንም አይነት ርምጃ አለመውሰዱን ገልፀዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ታጣቂዎቹ በየጊዜው ጥቃት በመጣል ልጆቻችንን አፍነው ሲወስዱ መንግሥት ድርድር ይካሄድ ከማለት በስተቀር እርምጃ ለመውሰድ እና አካባቢውን ከጥቃት ለመከላከል ዝግጁ አይደለም ሲሉ ያማርራሉ። የጋምቤላ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሕጻናቱን ለማግኘት ጥረት ላይ መሆኑን ተናግሯል።

”አኝዋ ሰርቫይቫል” የተባለው የጋምቤላ ሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ለዶቼቬለ በላከው መረጃ መሰረት ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሊ ታጣቂዎች መጋቢት አንድ ምሽት ላይ በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ጉድ ወረዳ ኦባዋ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት ነዋሪዎችን ገድለዋል ህጻናትንም አፍነው ወስደዋል። መንግሥት ምንም አይነት ርምጃ ባለመውሰዱ ታጣቂዎቹ ከአንድ ቀን በኋላ የመንግሥት የጥበቃ ኃይላት ብዙም ሳይርቁ በሚገኙበት ጆር ወረዳ አንጌላ ቀበሌ በከባድ መሣሪያዎች ተጨማሪ ሰዎችን ገድለዋል፣ ሕጻናትም አፍነው ወስደዋል ንብረትም አውድመዋል ሲሉ የድርጅት ኃላፊ ኒኪያው ኦቻላ ገልፀዋል።

”በመጀመሪያ ደረጃ የካቲት ወር አካባቢ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ታጣቂዎች ኦትዊልን በማጥቃት ስምንት ሰዎችን ገድለዋል። ከዚያ በኋላ 18 የሚሆኑ ሕጻናትን አፍነው ወስደዋል። ይሄ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ነገር ግን በከፋ መልኩ ሁለት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንጌላና ኦባዋ በሚባል ተከታታይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህ ወቅት በአንጌላ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ፣ አራት ሕጻናት ታፍነው ተወስደዋል። ኦባዋ ላይም በከፋ መልኩ ንብረቶች ወድመዋል፤ መንደር በአጠቃላይ ተቃጥሎአል፤ በዚያ ወቅት የሞቱት ሰዎች ከ18 በላይ ይሆናሉ የሚል መረጃ ነው የደረሰን። 22 ሕጻናቶች ታፍነው ተወስደዋል፤ እስካሁን ግን የመንግሥት ምላሽ ይህ ነው ማለት አይቻልም። ዝምታው ለምን እንደሆነ የሚገርም ነገር ነው።”

በእሁድ ዕለቱ ጥቃት ከ60 በላይ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን በጋምቤላ አስተዳደር የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ ፔተር ገብርኤል ገልፀዋል።

 

Gambela
ከ60 በላይ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል

 

”በርግጥ እሁድ ዕለት ማታ ኦባዋ በሚባል ቀበሌ የሙርሊ ታጣቂዎች ወደ 13 የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል፤ 21 የሚሆኑ ሕጻናት ታፍነው በሞርሊ ተወስደዋል። 60 የሚሆኑ ቤቶች ተቃጥለዋል። ነገሩ አሳዛኝ ነው።” ከደቡብ ሱዳን የሚመጡት የሙርሊ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ያደረሱት ጥቃት ያስታወሱት የአኝዋ ሰርቫይቫል ድርጅት ኃላፊ ኒኪያው ኦቻላ መንግሥት ስለ ባለፈው ሳምንቱ ጥቃትና ስለ ታፈኑት ሕጻናት ጉዳይ የገለፀው ነገር የለም ይላሉ።

”በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን እስካሁን ስለ ጋምቤላ፣ ስለአኝዋክ ብሔረሰብ የሞቱ ሰዎችና የታፈኑ ሕጻናቶች በምን አይነት መንገድ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደሚመለሱ መንግሥት ያወጣው መግለጫ የለም። እና ይህ ትንሽ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው ብዬ ነው የማምነው።” ይህን ችግር በድርድር ከመፍታት ይልቅ መንግሥት እርምጃ ቢወስድ ታጣቂዎች ወደ ቦታው ዳግም ባልመጡ ነበር ያሉት፤ በጋምቤላ አስተዳደር የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ገብርኤል ነዋሪው የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

”የሙርሊ ታጣቂ ኃይል ከደቡብ ሱዳን ነው የሚመጡት፤ ለምን መንግሥት ዝም ይላል? ለምን እርምጃ አይወስድም? ተደራጅተውና ድንበርን አቋርጠው እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ሲገባ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው። ሁልጊዜ የሚደረግላቸው ድርድር ነው፤ ስለዚህ በሙርሊ ላይ እርምጃ ካልተወሰደ ጥቃታቸውን መቼም አይተውም። ሕዝቡ አሁን ተሰዶ ሜዳ ላይ ነው ያለው። ስለዚህ የመንግሥት ቁጥጥር ላልቶአል።

የድንበር አዋሳኝ በሆኑ የጋምቤላ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር እየሠራ መሆኑን የገለፁት በጋምቤላ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኦሞት ኦቶዎ በበኩላቸው፤ ሁኔታው በመረጋጋት ላይ ነው፤ የመንግሥት ሠራዊት እየተከታተለ ነው። ”ከሃያ በላይ ታፍነው የተወሰዱት ሕጻናትስ ጉዳይ እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኦሞት ኦቶዎ፤ ”ሕጻናቱ ያሉበት ቦታ አይታወቅም ገና አልተገኙም” ባለፈውም ጊዜ ከመቶ በላይ ሕጻናት ታፍነው ተወስደው ነበር፤ 90 ሕጻናት ተመልሰው 40 ሕጻናት ቀርተዋል። አሁን ግን የታፈኑት ሕጻናት 22 ናቸው። አዲስ ነገር ካገኘን ይፋ እንናገራለን።”

መንደር ቀውድመው ሕጻናትን እያፈኑ ወስደው የሚሸጡት የሞርሊ ታጣቂዎች ቀደም ባሉት ዓመታት የቀንድ ከብትን ለመዝረፍ ብቻ ነበር ሲሉ በጋምቤላ አስተዳደር የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ ፒተር ገብርኤል ተናግረዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ