Cyber attack in Ethiopia

ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የሳይበር ጥቃት በ13 እጥፍ እንደጨመረ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አስታውቋል

የሳይበር ጥቃቱ በ13 እጥፍ ጨምሯል፤ ከ238 ሚሊዮን ብር በላይ በአገር ላይ ይደርስ የነበር ኪሳራ ማዳን ተችሏል

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 7, 2019)፦ በኢትዮጵያ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የሳይበር ጥቃት በ13 እጥፍ እንደጨመረ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አስታውቋል። ኤጀንሲው ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው የጥቃቱን ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት አስመልክቶ ይፋ እያደረጋቸው ካሉት መረጃዎቹ እንደሚያመለክቱ፤ በ2012 በጀት ዓመት ብቻ የሳይበር ጥቃቱ መጠን 791 መድረሱ ነው።

ከስድስት ዓመታት በፊት በ2005 አጠቃላይ አገራዊ የሳይበር ጥቃት መጠኑ 59 ብቻ እንደነበረም አመልክቷል። ይህ ግን በ6 ዓመት ውስጥ ከ13 እጥፍ በላይ በማደግ በ2011 ዓ.ም. 791 ደርሷል። በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ዝግጁነትና ምላሽ መስለጫ ማዕከል (Ethio-CERT) ምላሽ የተሠጠባቸው አገራዊ የሳይበር ጥቃቶች ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የሳይበር ጥቃቶች በእጅጉ እየጨመሩ መምጣታቸውን ነው።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የብሔራዊ የሳይበር ደኅንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ምክንያት በማድረግ፤ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የፓናል ውይይት ላይ እንደተመለከተውም የሳይበር ጥቃቶች እድገት አሳሳቢ መኾናቸውን ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመምጣቱ ተጨማሪ ማሳያ ኾኖ የሚጠቀሰው ሌላው የኤጀንሲው መረጃ፤ በ2012 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በሦስት ወሮች ውስጥ የደረሰው የሳይበር ጥቃት ነው። እንደመረጃው በሦስቱ ወራት በኢትዮጽያ 113 የሳይበር ጥቃቶችና ሙከራዎች ተደርገዋል። ይህ አኀዝ ከስድስት ዓመት በፊት በአንድ ዓመት ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ሲነፃፀር እንኳን በዚህ በጀት ዓመት በሦስት ወር የደረሰው ጥቃት ከእጥፍ በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው።

የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት 113 በተለያዩ ቁልፍ የአገሪቱ ተቋማትና መሠረተ-ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶችና ሙከራዎች ስለመከሰታቸው የሚያመለክተው መረጃ፤ በአገሪቱ ከተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች መካከል በቀዳሚነት የተቀመጠው በአጥፊ ሶፍትዌሮች (ማልዌር) ጥቃቶች ናቸው። በድረገጽ ላይ የተደረቱ ጥቃቶች ደግሞ 29 መኾናቸውን አስታውቋል። በመሠረተ-ልማት ቅኝቶች 22፣ ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ መግባት 13 እና የሳይበር መሠረተ-ልማቶችን ሥራ ማቋረጥ ደግሞ 7 ጥቃቶች መከሰታቸውን ይኸው የ2012 በጀት ዓመት የሦስት ወር የሳይበር ጥቃትን የተመለከተው የኤጀሲው መረጃ አመላክቷል።

በዲቪዥኑ ይፋ በተደረገው መረጃ በአገሪቱ ለተከሰቱ ሁሉም ዐይነት የሳይበር ጥቃቶች ምላሽ መሠጠቱንና ጥቃቶቹ ከመፈጠራቸው በፊት ገና ቅኝት ላይ እያሉ መቅጨትና የተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶችም ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት መግታት መቻሉን ግን ኤጀንሲው ገልጿል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አዘጋጅነት ሰሞኑን በተካሄደው ፓናል ላይ በሳይበር ደኅንነት ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶች፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ እየተሠራ ስላሉ ሥራዎችና የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ ስለሚኖረው ፋይዳ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ይህንኑ ውይይት በተመለከተ ኤጀንሲው በፌስቡክ ገጹ ካሰፈራቸ መረጃዎች ውስጥ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ረዳት ፕሮፌሰር ሔኖክ ሙሉጌታ ያቀረቡት ጽሑፍ በተቋማት ላይ ከሚደርሱ የሳይበር ደኅንነት ጥቃቶች 45 በመቶ የሚሆኑት የሚፈፀሙት በውስጥ የተቋማት ሠራተኞች መኾኑን በተደረገ ጥናት ማረጋገጥ የሚችል መሆኑን ይጠቁማል።

የኤጀንሲው የሳይበር ጥናት ዲቪዥን ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን ጓዴ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ ደግሞ፤ በዚህ ወቅት በዓለማችን ካሉ አሳሳቢ ጥቃቶች ውስጥ የሳይበር ጥቃት 5ተኛውን ደረጃ እንደያዘ መናገራቸውን ይኸው የኤጀንሲው መረጃ ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ ካሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ውስጥ አብዛኞቹ የልማት ሥራዎች የሳይበርን ደኅንነት ታሳቢ ያላደረጉ መኾናቸውን እንዳመለከቱ ያስረዳል። ተቋማት ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ደረጃዎችን አለማሟላት፤ ተቋማት ለሳይበር ደኅንነት ማስጠበቂያ የሚሆን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሌላቸው ሆኖ መገኘት ለሳይበር ጥቃቱ ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ ካደረጉ ምክንያቶች መሐል የሚጠቀስ ስለመኾኑ የዶ/ር ሰለሞን ጽሑፍ አመልክቷል።

ከዚህም ሌላ አብዛኞቹ የልማት ሥራዎች የሳይበርን ደኅንነትን ታሳቢ ያላደረጉ መሆን፣ ተቋማት ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ደረጃዎችን አለማሟላት፤ ተቋማት ለሳይበር ደኅንነት ማስጠበቂያ የሚሆን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሌላቸው ሆነው መገኘትም እንደ ክፍተት የሚታይ ነው። በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሳይበር ደኅንነት ላይ ማስተማር የሚችሉ ሙያተኞች እጥረት ያለባቸውና የበጀት ውስንነት እንደ አገር ያሉ ችግሮች መሆናቸውንም መረጃ አመልክቷል።

የሳይበር ደኅንነት ንቃተ-ሕሊና ጥናት ውጤት
የሳይበር ደኅንነት ንቃተ-ሕሊና ጥናት ውጤት

እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ግን ኤጀንሲው የኮምፒዩተር ወንጀል መቆጣጠሪያ ሕግ ማውጣትን፣ የተለያዩ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች መሠራታቸውን፣ በተለያየ ደረጃ የደኅንነት መሠረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸው ተጠቅሷል። በተገነቡ መሠረተ ልማቶች የአፈጻጸም፣ የኦዲትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም ጥቃቶች ሲደርሱ የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የተጎዱ ፋይሎችን ወደነበሩበት የመመለስ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ዶ/ር ሰለሞን መጥቀሳቸውን ኢመደኤ ገልጿል።

በዚህ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ሳይበር ጥቃት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፤ ሕብረተሰቡ ከምንጊዜውም በላይ ለሳይበር ደኅንነት ትኩረት እንዲሰጥ ሰሞኑን እየተካሄደ ያለውና የአንድ ሳምንት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አንዱ በሆነው የፓናል ውይይት ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤፍራህ አሊ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልእክት አስተላልፈዋል። አክለውም፤ በአገራችን ከዓመት ዓመት እየደረሱ ያሉት የሳይበር ጥቃቶች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በመኾኑም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከምንጊዜውም በበለጠ ለሳይበር ደኅንነት ትኩረት ሊሠጥ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል። የሳይበር ጥቃቶችን በማክሸፍ ለሳይበር ጥቃት ወቅታታዊ ምላሽ በመሥጠት፤ የተሠራው ሥራ ጥሩ አፈጻጸም የታየበት ሲሆን፤ በተጠናቀቀው 2011 የበጀት ዓመትም ከ791 በላይ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፍ መቻሉን ጠቁመዋል። በሌላም በኩል የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀልን በመከላከል ረገድ፤ በአገር ላይ ይደርስ የነበረውን ከ238 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ማዳን መቻሉንም የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።

ኾኖም ጥቃቱን ለመከላከል ተቋማትም ሆኑ ኤጀንሲዎች ትኩረት ሠጥተው መሥራት እንደሚኖርባቸው በሰሞኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!