NISS and Cyber_Horus Group

የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) እና ሳይበር ሆረስ ግሩፕ (Cyber_Horus Group)

ጥቃቱ መክሸፉን ኢትዮጵያ አሳውቃለች
ዓላማው ከግድቡ የውኃ ሙሌት ጋር የተያያዘ ነው

ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 23, 2020)፦ መቀመጫቸውን ግብጽ ያደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) አስታወቀ።

ኤጀንሲው እንዳስታወቀው የሳይበር ጥቃቶቹ ተቃጥተው የነበሩት፤ ሳይበር ሆረስ ግሩፕ (Cyber_Horus Group)፣ አኑቢስ ዶት ሐከር (anubis.hacker) እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ (Security By Passed) በተባሉ ጥቃት አድራሾች ነው።

ከሰኔ 10 እስከ 14 ባሉት ተከታታይ ቀናት በእነዚህ ወንጀለኞች የተቃጡት የሳይበር ጥቃቶች በአሥራ ሦስት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማትና አራት መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት ድረ ገጾችን የማስተጓጎል ሙከራ ተደርጓል።

የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው አብዛኖቹ በድረ ገጽ ግንባታ ሒደት ደኅንነታቸው ታሳቢ ያላደርጉ ተቋማት፣ የደኅንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት የነበራቸው መኾኑንም የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።

እነዚህ ጥቃቶች በኤጀንሲው መከላከል ባይደረግ ኖሮ በአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበርም ሳይገልጽ አላለፈም።

ኤጀንሲው በመግለጫው ያመለከተው በግብሽ ጥቃት አድራሽ ቡድኖች ኃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን፤ ዋና ዓላማቸው ከህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተለይ በውኃ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ በአገሪቱ ላይ ለመፍጠር በማሰብ እንደተፈጸመ ነው ያስታወቀው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ