Nobel Laureate PM Abiy Ahmed and the First lady

ኖቤል ሎሬት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኦስሎ ግራንድ ሆቴል ደስታቸውን ሊገልጹ ለመጡ አድናቂዎች ሰላምታ ሲሰጡ

ኢትዮጵያ የገነነችበት ቀን

ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 11, 2019)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና የሚሠጠውን የኖቬል ሽልማት (የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት) በኦስሎ በታላቅ ክብር ተቀብለዋል። ዕለቱ ኢትዮጵያ የገነነችበት ቀን ለመኾን በቅቷል።

ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኖርዌይ ርዕሰ ከተማ ኦስሎ በታላቅ ክብር በተደረገ የሽልማት አሠጣጥ ሥነሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዚህ ሽልማት መብቃት በዋናነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ሞት አልባ ጦርነት በሰላም መፍታት መቻላቸው ነው።

በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ያሉ ልዩነቶችን በመፍታትና ጠቅላይ ሚኒስትር በኾኑባቸው በመጀመሪያዎቹ መቶ ቀናት የወሰዱዋቸው ወሳኝ እርምጃዎች ሰላም ከማስፈን አንጻር ያስገኙት ውጤት ጭምር ታስቦ ለዚህ ክብር እንዳበቃቸው ተገልጿል።

የሽልማት አሠጣጥ ሥነሥርዓት ላይ ኢትዮጵያን የተመለከተን ታሪካዊ እውነታዎች በሽልማት ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ቤሪት ሬስ-አንደርሰን የተገለጸበት መንገድ፤ ዓለም ኢትዮጵያን የበለጠ እንዲያውቃት ያስቻለ ነበር።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን በመጥቀስ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ “ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን!” ሲሉ ወይዘሮዋ በገለጹበት ወቅት፣ የፕሮግራሙ ታዳሚዎች የሞቀ ጭብጨባ የቻሩ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ባሻገር ኢትዮጵያ ከፍ ብላ እንድትገለጽ ያስቻላት ክስተት ኾኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ያደጉት ንግግርም ቢሆን ኢትዮጵያን ያስተዋወቀ ነበር። ሽልማቱን ለእርሳቸው ብቻ የተሠጠ ያለመሆኑን እንዲሁም ለዚህ ሽልማት የበቁት በእርሳቸው ጥረት ብቻ ሳይሆን በኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጭምር በመኾኑ፤ መድረኩ እውቅና ሊሠጣቸው ይገባል ብለዋል።

ከሽልማት አሠጣጡ ፕሮግራም በኋላ፣ ምሽት ላይ፤ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና ኖርዌጅያን አንድ ላይ ኾነው ከግራንድ ሆቴል ፊት ለፊት ደስታቸውን በገለጹበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ጋር ኾነው ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የኦስሎው ፕሮግራም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይገባቸዋል!” የሚለውን አመለካከት እንዲቀበሉ ያደረገ ነው። የኖቬል ሽልማት አሸናፊ መኾናቸው ከተገለጸበት ጊዜ በላይ፤ የሽልማት ፕሮግራሙና አጠቃላይ ክንውኑ ዶክተር ዐቢይ የበለጠ ተቀባይነት ያገኙበት መሆኑን በጉዳዩ ላይ የተሠጡ አስተያየቶቹ ያመለክታሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኦስሎ የኖቬል ሽልማትን ከተቀበሉ በኋላ፣ አንዲሁም ማምሻው ላይ በግራንድ ሆቴል ተሰብስበው ደስታቸውን ለገለጹ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና ኖርዌጅያን ምስጋና ያቀረቡበትን መልእክት አስተላልፈዋል። በዚህ መልእክታቸው የኖቬል ሽልማቱ ያለውን አንደምታ ያንጸባረቁበትም ነበር። መልእክቱ የሚከተለው ነው።

ኢትዮጵያ የገነነችበት ቀን ከማኅደረ ጆ

ኢትዮጵያውያን በዘመናት ታሪካቸው እጅግ ከኮሩባቸው ተጠቃሽ ክስተቶች ውስጥ ዛሬ በኦስሎ ዓለም እንዲያውቀው የኾነው እውነት አንዱ ስለመኾኑ ብዙዎች ይስማሙበታል።

የዓለማችን ቀዳሚ የእውቅና መጐናፀፊያ በመኾን በሚጠቀሰው ታላቅ መድረክ ላይ ታላቁን የኖቬል ሽልማት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተቀበሉ። በእርሳቸው በኩልም ኢትዮጵያ ተሸለመች። ያውም በሰላም!

ይህ ከታላቅ ክብር ጋር የተሠጠ ሽልማት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ገኖ እንዲሰማ ያደረገ፣ የኢትዮጵያውያንን ጮቤ ያስረገጠ ታሪክ የታየበት ቀን ነው።

ስለኢትዮጵያውያንና ስለኢትዮጵያ ዓለም እንዲያውቅ፣ ታሪኳ በዚህ መድረክ እንዲነበብ እድል የሠጠ፣ በክብር ያስተዋወቀ በዘመናት ውስጥ የሚገኝ ወርቃማ አጋጣሚ የፈጠረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ስለሰላም አበርክቷቸው ያገኙት የክብር ሽልማት የአገራቸውን ስም በክብር እንዲጠራ በማድረግም እንደ ልዩ ቀን ሊታሰብ የሚገባውም ቀን ነው።

ይህ የሽልማት ፕሮግራም በቀጥታ በሚተላለፍበት ሰዓት ከየአቅጣጫው በማኅበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ሲስተጋቡ የነበሩ የተለያዩ አስተያየቶችና መረጃዎች፤ በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ የሚፈጥሩት መልካም እድል ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ የሚሠጥ ነው። ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሽልማቱ ፕሮግራምና አጠቃላይ ይዘት ላይ የተደመሙ ሁሉ የሠጡት አስተያየት ይህንኑ የሚያመላክት ነው።

ታዋቂ ሰዎች በኢትዮጵያዊነታቸው መኩራታቸውን አጉልተው ያሳዩበትን አስተያየቶቻቸው እንዲሰነዝሩ ያስቻለም ነው። በጽንፈኝነታቸው የሚታወቁ ታዋቂ ሰዎች ሳይቀሩ “እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አለዎ!” እንዲሉ ያስገደደ ጭምር ነው።

ከዘመናት በኋላ አብዛኛው ሕዝብ ተመሳሳይ መልእክት ያስተላለፈበት ክስተት አለ ከተባለ ከዛሬው የኖቬል ሽልማት በላይ ሊኖር እንደማይችል ይገመታል።

ከዚህ ክብር በተቃራኒ ሊቆም የሚችል ይኖራል ተብሎ ለማሰብ ቢከብድም፤ የሆነው ነገር ግን ይህንን ስሜት በማውጣት እንኳን ደስ አለን ያስባለ ነው።

የኖቤል ሽልማቱን አስመልክቶ የተደረገ ተቃውሞ

ኦስሎ ከተማ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚነትን አስመልክቶ ከፍተኛ ድጋፍና ደስታን ብታስተናግድም፤ አንዳንድ ወገኖች በተለይም የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ በሕወሓት አቀንቃኝነትና አስተባባሪነት የተወሰኑ ግለሰቦች ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ከኦስሎ የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኖርዌይ ነዋሪ የኾኑ የሕወሓት ደጋፊዎች የኖቤል ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለሙን ከመቃወማቸው ባሻገር፤ የኤርትራን ባንዲራ በመያዝ በኢሳይያስ አፈወርቂ መንግሥት ላይ የኢኮኖሚና የሚሊተሪ ማዕቀብ እንዲጣልና በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ ጠይቀዋል። ከዚህም ባሻገር በሌብነት ወንጀል (ሙስና) የተከሰሱት የሜቴክ ኃላፊ ጄኔራል ክንፈ ዳኜው ከእስር እንዲለቀቁ መጠየቃቸው ታውቋል። (ኢዛ)

ሙሉውን ታሪካዊ የሽልማት ሥነሥርዓት ለመመልከት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!