Adanech Abiebie

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

በአዲስ አበባ ባለቤት ያልተገኘላቸው ሕንጻዎች 100 ደርሰዋል

ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 19, 2020)፦ በአዲስ አበባ ባለቤት አልባ ናቸው የተባሉ ሕንጻዎች ቁጥር አንድ መቶ መድረሱን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ወ/ሮ አዳነች ይህንን አስገራሚ መረጃ የሰጡት ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ውይይት እያደረጉ ባሉበት መድረክ ላይ ነው።

በዚህ ውይይት ላይ በከተማዋ አለ ስለሚባለው የመሬት ወረራና ባለቤት አልባ ስለሚባሉ ሕንጻዎች የጠቀሱት መረጃ ይገኝበታል።

እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ የከተማው አስተዳደር ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 100 የሚኾኑ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሕንጻዎች ባለቤት ያልተገኘላቸው መኾኑ ስለመረጋገጡ ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ከእነዚህ ሕንጻዎች ሌላ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ታጥሮ የተቀመጡ ከአንድ ሺህ ሔክታር መሬት በላይ ባለቤት ሳይገኝላቸው መቅረቱንም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕገወጥ የኾነ ሥራ ሲሠራበት ነበር ተብሎ በሚታመነው የቀበሌ ቤቶች ጉዳይ ላይም ወይዘሮ አዳነች እንደገለጹት ከኾነ፤ በእነዚህ የቀበሌ ቤቶች ላይ የማጣራት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ያለው የመሬት ወረራ ላይ ምን አስተያየት እየተሰጠ ነው?

ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በውስን የከተማዋ ክፍለ ከተሞች ባደረገው ጥናት ከ200 ሔክታር መሬት በላይ በሕገወጥ መንገድ መወረሩን ካስታወቀ በኋላ፤ ባለፈው ወር ጥቅምት መጨርሻ ሳምንት ላይ የከተማው አስተዳደር ባደረግኩት የማጣራት ሥራ ከ460 ሔክታር መሬት በላይ በሕገወጥ መንገድ የተያዘ መሬት አግኝቻለሁ ብሎ ማስታወቁ አይዘነጋም።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባለፈው ወር ጥቅምት መጨረሻ ሳምንት ላይ ከሰጡት መግለጫ መረዳት እንደተቻለው ከተማዋ ውስጥ ተፈጸመ የተባለውን የመሬት ወረራ ለማጣራት አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ባደረገው ማጣራት ከ460 ሔክታር መሬት በላይ በሕገወጦች ተይዞ መገኘቱን ገልጸው ነበር። በዛሬው ዕለት ደግሞ ከአንድ ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በሕገወጦች መያዙን ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በከተማ የመሬት ወረራ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ በአስተዳደሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ወደ ማጣራት ሥራ እንዲገባ የተደረገው በከተማዋ ውስጥ የመሬት ወረራ እየተፈጸመ ስለመኾኑ ጥቆማና ቅሬታ በመቅረቡ ነው። ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ውስጥ በፓርቲ ደረጃ ባልደራስና ኢዜማ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።

ግብረ ኃይሉ በመሬት ወረራ ዙሪያ አሁን ደረስኩበት ያለውና በከንቲባዋ በኩል ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ይፋ የተደረገው መረጃ በዝርዝር መረጃ የታገዘ ባይኾንም፤ ግብረ ኃይሉ 460 ሔክታር መሬት በሕገወጦች ስለመያዙ አረጋግጫለሁ ማለቱ በራሱ የሚናገረው ነገር ነበር። በዛሬው ዕለት ከአንድ ሺህ ሔክታር በላይ በሕገወጥ መንገድ መያዛቸው ማረጋገጫ የተገኘላቸው መሬቶች በእነማን እጅ እንደነበሩ የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ምክትል ከንቲባዋ ያሉት ነገር የለም።

በጥቅምቱም ኾነ በዛሬው የአስተዳደሩ መረጃ ላይ አንዳንድ ወገኖች በከተማዋ ውስጥ እየተፈጸመ ከነበረው ሕገወጥ የመሬት የወረራና ባልተገባ መንገድ ይሰጥ ነበር ተብሎ ከሚገመተው መሬት አንጻር በሕገወጦች ተያዘ ተብሎ የተገለጸው የመሬት መጠን አነስተኛ ነው የሚል አመለካከት ማሳደሩ አልቀረም።

እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው ወገኖች እየተሰጠ ያለውም አስተያየት አዲስ አበባ በሕገወጦች እና በተፈራረቁበት ባለሥልጣናት የተመነተፈችው መሬት በአንድ ሺህ ሔክታር ብቻ የሚገለጽ ያለመኾኑን ነው። በቅርቡ ኢዜማ ባደረገው ጥናት እጅግ ውስን በኾኑ ክፍለ ከተሞች (ወደ አምስት ክፍለ ከተሞች) በሕገወጥ መንገድ ተይዟል ብሎ የገለጸው 200 ሔክታር መሬት መወረሩን ነው። ስለዚህ በውስን ቦታ በተደረገ ፍተሻ ኢዜማ ይህንን ያህል መሬት በሕገወጦች መወረሩ ከተገለጸ፤ የአስተዳደሩ ግብረ ኃይል በድፍን ከተማዋ አገኘሁ ያለው በሕገወጦች የተያዘ የመሬት መጠን አነስተኛ ነው የሚለውን እምነታቸውን ይገልጻሉ።

በቁጥር ደረጃ አስተዳደሩ ያመለከተውም ኾነ ኢዜማ ደረስኩበት ያለው መደምደሚያ እንደተጠበቀ ኾኖ አሁን የከተማዋ አስተዳደር መግለጫ የተሰጠበት በሕገወጦች ተያዘ የተባለው መሬት መጠን የአዲስ አበባ የመሬት ወረራና ሕገወጥ ተግባራት የከፋ ስለመኾኑ የሚያሳይ እንደኾነ በግልጽ የሚያሳይ መኾኑን ያረጋግጣል።

ወይዘሮ አዳነች በሰጡት መግለጫ ግብረ ኃይሉ ደረሰበት ያሉት ሌላው እውነት ደግሞ ለሕገወጥ ወረራው መስፋፋት የአስተዳደሩ ሠራተኞች እና ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት መጠቆሙ ነው።

በዚህ ዙሪያ በተለይ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ከሰጡት ማብራሪያ መገንዘብ እንደሚቻለው፤ በመሬት ወረራ ውስጥ ተሳታፊ ኾነው የተገኙት በርካታ አካላት ቢኾኑም፤ በተለይ የከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ቀዳሚ የችግሩ መንሥኤ መኾናቸውን ማመናቸው መልካም ነገር ነው።

እነዚህ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ብቻ ሳይኾኑ በዚህ የመሬት ወረራ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠቀሱት በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ ታቅፈው የሚንቀሳቀሱ ጭምር እንደሚገኙበት መጠቀሱ ጉዳዩን አስገራሚ አድርጐታል። በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ወይዘሮ አዳነች በመሬት ወረራው ትላልቅ መሬቶችን አጥረው ካስቀመጡት ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትም አሉበት ቢሉም፤ የእነዚህን ማንነት አለመጥቀሳቸው ግን አሁንም በወረራው ዙሪያ የሰጡት መረጃ የተሟላ ያለመኾኑን ያሳያል።

እንደ ምክትል ከንቲባዋ ገለጻ ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሚመስሉ በተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ሰፋፊ የመንግሥት መሬት አጥረው ተገኝተዋል ካሉ እነማን? የሚለውንም መመለስ ነበረባቸው።

ከከንቲባዋ የጥቅምቱ ወር ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው ግን፤ ሕገወጥ የመሬት ወረራ እንዲስፋፋ በማድረግ የአስተዳደሩ ሠራተኞች መሬት እንዴት እንደሚዘረፍ ለአዲስ ባለሥልጣናት ሳይቀር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ ኾነው መገኘታቸውን መመልከታቸው ነው።

እነዚህ እስከ ኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ የአስተዳደሩ ሠራተኞች አንድ ባለሥልጣን ከኃላፊነቱ ተነስቶ በአዲስ ሲተካ፤ እነዚህ ሠራተኞች መሬት እንዴት እንደሚዘረፍ ያመላከቱና ሁኔታዎችን ያመቻቹ እንደነበር ሁሉ ምክትል ከንቲባዋ ገለጹ መባሉም በራሱ እንደ ትልቅ መረጃ የሚታይ ነው። ይህ ከታወቀ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ በመሬት ወረራ ላይ ኤክስፐርት መኾናቸው የተነገረላቸውና የሚወረሩ መሬቶችን የሚያመቻቹ መኖራቸው ከተረጋገጠ፤ በቀጣይ የሚጠበቀው እርምጃ በእርግጥ በሕገወጥ መንገድ ተያዙ የተባሉት መሬቶች ወደ መሬት ባንክ ማስገባት አንድ ነገር ኾኖ፤ በሕገወጥ መሬት ወረራው ፊት አውራሪዎች አሁንም ቦታቸው ላይ ካሉ ከንቲባዋ ምን ዐይነት እርምጃ ወስደው ይኾን? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ።

መቼም በሕገወጥ የተያዙት መሬቶች ወራሪዎቹ ሊታወቁ ይችላሉና እነርሱ ላይስ ምን እርምጃ እንደሚወሰድ ሕዝብ ማወቅ ይፈልጋልና የሕገወጥ ተግባሩን የመግለጽ ብቻ ሳይኾን ሕገወጥ ተግባሩን ስለፈጸሙት ሰዎች መጨረሻም ሊነገረን ይገባል የሚሉ ከተማዋ ነዋሪዎችና ዜጎች በርካቶች ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!