Total coronavirus cases in Ethiopia, Feb. 22, 2021

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ሰኞ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም.)

በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ድጋሚ እየጨመረ ነው
ከሁለት ሺሕ ሰዎች በላይ በበሽታው ሞተዋል

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 22, 2021)፦ በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 (ኮሮና ቫይረስ) ወረርሽኝ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለመምጣቱ እየታየ ነው። በበሽታው ተይዘው ከሚሞቱ ሰዎች ውስጥ የወጣቶችም ቁጥር እንደጨመረ፣ ጽኑ ታማሚዎችም ከወትሮ በተለየ ቁጥር ከፍ እያለ ነው። እስካሁን በበሽታው ተጠቅተው ሕይወታቸው ማለፉ ከተገለጹት ታዋቂ ሰዎች መካከል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ይጠቀሳሉ። ትናንት ደግሞ የዓለም ሎሬት ጥበበ የማነብርሃን በዚሁ በሽታ ተይዘው ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እንዲህ ካሉ መረጃዎች አንፃር የኮቪድ 19 በሽታ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚጠቁም ነው።

ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር መልሶ እያሻቀበ ስለመምጣቱ የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ መረጃ እያሳየ ነው። በበሽታው ተይዘው የሚሞቱ ሰዎችም ቁጥር በተመሳሳይ እየጨመረ መሔዱን ከዚሁ አኀዛዊ መረጃ መገንዘብ እየተቻለ ነው።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት አሥራ አንድ ወሮች በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ153 ሺሕ 541 በላይ ደርሷል።

በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል በሕብረተሰቡ ዘንድ እየተደረገ ካለው የጥንቃቄ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ፤ በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ለመምጣቱ የጤና ሚኒስትር ሪፖርት እያሳየ ነው።

ከጤና ሚኒስትር ተከታታይ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው፤ በበሽታው ተይዘው የሚሞቱና በጽኑ ሕመም ላይ የሚገኙት የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ጨምሯል።

የጤና ሚኒስትር የሦስት ወር አኀዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩ፤ በታኅሣሥ ወር በአማካይ ከ500 በታች ይመዘገብ የነበረው የታማሚዎች ቁጥር፤ በጥር ወር በአብዛኛው በየዕለቱ ከ600 – 700 ይመዘገብ ነበር።

በየካቲት አጋማሽ ላይ በዕለት የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ800 በላይ ደርሷል። የካቲት 13 ቀን ያወጣው ሪፖርትም በ24 ሰዓት 841 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። በተመሳሳይ ትናንት የካቲት 14 ቀን በወጣው ሪፖርት ደግሞ 949 ሰዎች፣ ዛሬ ደግሞ 735 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

በታኅሣሥ 2013 ዓ.ም. በአማካይ ከአምስት መቶ ያነሰ ቁጥር የተመዘገበበት በቫይረሱ የተያዙ ቁጥር በቀጣዮች ሁለት ወራት ግን ከ600 እና 700 በላይ የሚኾን ቁጥር እየተመዘገበ መጥቶ በየካቲት ወር ከ800 በላይ ሊደርስ ችሏል።

የጽኑ ሕሙማን ቁጥርም በማደግ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በጽኑ የታመሙ በሽተኞች ቁጥር 337 ደርሷል። ዕለታዊ የመቶኛ ቁጥርም 12 ደርሷል።

ዛሬ ይፋ በኾነ መረጃ መሠረት በየካ ኮቪድ ሕሙማን ማዕከል ከሚገኙ የጽኑ ሕሙማን መካከል በአማካይ ከአሥሩ ስምንቱ እየሞቱ መኾኑን ማዕከሉ አስታውቋል።

ከቀን ወደ ቀን በቫይረሱ ተይዘው ወደ ጽኑ ሕሙማን የሚገቡ ሕመምተኞች ቁጥር መበራከቱን ማስታወቁም በሽታው የብዙዎችን ሕይወት ሊቀጥፍ የሚችል መኾኑን እያመለከተ ነው።

እስከ ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ባለው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር ከ2.096 ሚሊዮን በላይ ነው። ከዚህ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው 153,541 ሲሆን፣ ሕይወታቸው ያለፈ ደግሞ ከ2,293 በላይ ኾኗል።

ከቫይረሱ ያገገሙ ደግሞ 131,713 ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ቫይረሱ ያለባቸው 19,533 መድረሱን ያመላክታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ