PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

“ጁንታው የሚሰጠውን በጀት ከመከላከያ እኩል የኾነ ኃይል ለመገንባት አውሎታል” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ
ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ አደጋ ካልመጣ በስተቀር ከማንም ጋር ግጭት ውስጥ አንገባም

ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 5, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። ዛሬ ሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ተጠባቂ የነበረው የትግራይ ክልልና የተኩስ አቁም አዋጅን ጨምሮ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነበሩ።

በዛሬው ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ማብራሪያ የተወሰኑትን በሚከተለው መንገድ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል አጠናክሯቸዋል።

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ከገለጹት ውስጥ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው ድንገት ያለመኾኑን መግለጻቸው ተጠቃሽ ነው። የሠራዊቱ አወጣጥ የድንገት ሳይኾን መውጣት የጀመረው ከአንድ ወር በፊት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱን ከትግራይ ለማስወጣት የተወሰነው ታስቦበት እና ተመክሮበት እንደኾነም ያመለከቱ ሲሆን፣ የሠራዊቱን መውጣት ኢትዮጵያ ተዳክማለች በሚል የሚነዛው አሉባልታ መሠረት የሌለውና መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ለመስጠት እና ትግራይ አካባቢ ላለው አካልም የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ያለመ ውሳኔ መኾኑንም አመልክተዋል።

“ጁንታው የሚሰጠውን በጀት ከመከላከያ እኩል የኾነ ኃይል ለመገንባት አውሎታል”

ከወቅታዊ የትግራይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከሰጡት ማብራሪያ፤ የጁንታው ከዚህ ቀደም ይሰጠው የነበረውን በጀት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሊስተካከል የሚችል ኃይል ለመገንባት ያውለው እንደነበርም ገልጸዋል።

እንዲህ ያለ ኃይል ለመገንባትና ኃይላቸውን ለማጠናከር ሲሠሩ ከነበረው ሥራ ባሻገር፤ በተለያዩ ክልሎች ቅጥረኞችን ቀጥረው ገንዘብ በመመደብ ሌላውን የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይረጋጉ ሲያደርጉ እንደነበር አመልክተዋል።

የህዳሴ ግድብና የግጭት ሥጋት

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ፤ በህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያ ፍላጐት የኢትዮጵያን የመብራት ጥያቄ የሚመልስ መኾኑን አብራርተው፤ የሱዳንና የግብጽንም ሥጋት የሚቀንስ መኾኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ባሻገር በዚህ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ልትገባ ትችል እንደኾነ ለቀረበ ጥያቄ ደግሞ፤ “ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ አደጋ ካልመጣ በስተቀር ከማንም ጋር ግጭት ውስጥ አንገባም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሰላምና በትብብር መልማት፣ ማደግ እንደምትፈልግ ያከሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማደግ ስለምንፈልግ ሰላም እንፈልጋለን። ለሰላም የሚከፈል ማንኛውም ነገር እንከፍላለን ብለዋል።

ነገር ግን ሰላም መፈለጋችን ክብራችንና ሕልውናችንን የሚነካ ከኾነ ግን፤ ተገደን ሰላምን ለማምጣት የምንገባባቸው ግጭቶች ይኖራሉ በማለትም ተናግረዋል።

መንግሥት ካሉት ኤምባሲዎች ግማሹን ይቀንሳል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው የፓርላማ ቆይታቸው እንደ አዲስ ሊታዩ ከሚችሉ መረጃዎች መካከል፤ አገሪቷ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ካሏት ኤምባሳሲዎች ግማሽ ያህሉን የመቀነስ እቅድ ያላት መኾኑን ገልጸዋል።

ብዙ የሚባሉ አገሮች በኮቪድ 19 እና ጊዜው ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንጻር ኤምባሲዎቻቸውን እየዘጉ ስለመኾኑ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም ቢያንስ 30 ኤምባሲዎቿን እንደምትቀንስ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ኤምባሲዎች ምን ያህል ለኢትዮጵያ ጠቅመዋል? የሚለው ጉዳይም ጥያቄ ውስጥ መግባቱን አስገንዝበዋል። በመኾኑም ቀጣዩ መንግሥት በዚህ ዙሪያ የሚሠራ መኾኑንም አመልክተዋል። ዲፕሎማሲያችንን መፈተሽ አለብንም ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!