በገዳማይቱ ፌዴራል ፖሊስና ኢሣዎች ተጨፋጨፉ
Ethiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2000 ዓ.ም. March 10,2008)፦ በአፋር ክልል በምትገኘው ገዳማይቱ በተባለችው ኬላ ላይ በኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት በኢሣዎች እና በፌዴራል ፖሊስ ምክንያት በተነሳ ብጥብጥ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች ከሁለቱም ወገን መሞታቸው ታውቋል።
ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው ገዳማይቱ የተባለቸው አካባቢ ለኮንትሮባንድ ንግድ አመቺ በመሆኗ ነጋዴዎች በማስተላለፊያነት ይጠቀሙባታል። ጉምሩክ ባለሥልጣን በበኩሉ ገዳማይቱ ላይ የራሱ የሆነ መቆጣጠሪያ ኬላ ተክሏል።
በአካባቢው የሚገኙ የኢሣ ብሔረሰቦች ኬላው እንዲነሳ በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም ምላሽ ሳያገኙ በመቅረታቸው ከፖሊስ ጋር በተደጋጋሚ ሲተናኮሱ ቆይተዋል።
ባለፈው ሣምንት በአካባቢው በርካታ የኮንትሮባንድ ዕቃ ገብቶ ንግድ ልውውጥ በሚያደርጉበት ሰዓት የፌዴራል ፖሊስ ከቦ ተኩስ እንደከፈተባቸውና በምላሹ እነሱም በከፈቱት የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
ኢሣዎቹ ጫካ ውስጥ ጭምር የሚኖሩ በመሆናቸው ከየትም አቅጣጫ በሚመጡ መኪኖች ላይ ተኩስ በመክፈት መንገዱን ዘግተው የነበረ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በርካታ መኪኖችን አንድ ላይ በማድረግ የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አጅበው አሳልፈዋቸዋል። እንደምንጮቻችን ገለጻ ከሆነ ጭፍጭፉ አሁንም እንደቀጠለ ነው።



