በአተት የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
Ethiopia Zare (ሐሙስ ነሐሴ 21 ቀን 2001 ዓ.ም. August 27, 2009)፦ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ወይም በምህፃረ ቃል “አተት” ተብሎ በሚጠራው በሽታ የተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
በሽታው በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የተዛመተ ወረርሽኝ መሆኑን የገለጹት አንድ የራስ ደስታ ሆስፒታል ሐኪም፤ “በዚህም ምክንያት ሆስፒታሎች ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በሽታውን በተመለከተ የየራሳቸውን ክፍል አቋቁመዋል” ብለዋል።
በዕድሳት ላይ የሚገኘው ዘውዲቱ ሆስፒታልም ከነሐሴ 17 ቀን ጀምሮ የአተት ተጠቂዎችን እንዲቀበል የተደረገ ሲሆን፤ በ3 ቀናት ብቻ ከ1500 በላይ የበሽታው ተጠቂዎችን መቀበሉ ታውቋል። ከነዚህ መካከል ሁለት ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያመነ ሲሆን፤ በየሆስፒታሉ በሽተኞችን ለማስተናገድ የተመደበው ቦታ በቂ ስላልሆነ በቅጥር ግቢዎቹ ውስጥ በሚገኙት ክፍት ቦታዎች ላይ ድንኳኖች ተጥለው ታማሚዎች የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።
በራስ ደስታ ከአንድ ሺህ በላይ፣ በየካቲት 12 ከ500 በላይ፣ በሰሜን ሸዋ ደግሞ ከአንድ ሺህ በላይ፣ … በአጠቃላይ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆን ኢትዮጵያውያን በበሽታው ተጠቅተው በሕክምና ላይ ይገኛሉ። ወደየሆስፒታሉ ከሚያመሩ ታማሚዎች መካከል የተወሰኑ አልጋ ሲይዙ፤ ሌሎቹ በተመላላሽ እንደሚታከሙ የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።
“የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታውን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ አነስተኛ ነው” በማለት የሚተቹት የዘርፉ ባለሙያዎች በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በበቂ አላስተማረም፣ የመረጃ አሰጣጡም ደካማ ነበር ብለዋል። በሽታውን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዳልተቻለና በየቀኑ ከ100 በላይ ሰዎች ወደየሆስፒታሉ ሕክምና ለማግኘት እንደሚሄዱ ለመረዳት ተችሏል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ደብረ-ምጥማቅ ፃድቃኔ ማርያም አካባቢ በተከሰተው ተመሳሳይ በሽታ 21 ሰዎች እንደሞቱና 1500 ሰዎች ደግሞ ሕክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል ያቀኑ ሲሆን፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ሁኔታውን በስፍራው ተገኝተው ለመመልከት መሄዳቸው ታውቋል።



