በአተት ምክንያት ምግብ ቤቶች እየታሸጉ ነው
Ethiopia Zare (ኀሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2001 ዓ.ም. September 3, 2009)፦ በሀገሪቱ ውስጥ በቅርቡ የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ተውከት (አተተ) በሽታ ለመከላከል በሚል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአንዳንድ አገልግሎት ሰጪ የአዲስ አበባ ሆቴሎችንና ምግብ ቤቶችን በማሸግ ላይ መሆኑ ተገለፀ።
የእሸጋው ሂደት በአግባቡ አልተካሄደም የሚሉ ወገኖች እንደገለጹት፤ የሚኒስትር መ/ቤቱ በሽታው ተከስቶ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጐችን ከማጥቃቱና የተወሰኑትንም ከመግደሉ በፊት የሚጠበቅበትን የቅድመ መከላከል ርምጃ አልወሰደም የሚል ቅሬታ ቢያሰሙም፤ የጤና ጥበቃ አተት የተፈጠረው “ምግቦች ከመበከላቸው፣ አንዳንድ ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች የተሟላ ጽዳት የሌላቸው በመሆኑ ነው” ብሏል።
የመ/ቤቱ እምነት ይህ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ብዙዎቹ መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች ከምግብ ማብሰያና ማከማቻ ክፍሎቻቸው አጠገብ መፀዳጃ ቤቶች እንደሚገኙባቸው፣ መፀዳጃ ቤቶቹም የጽዳት ሠራተኞች አይተዋቸው የማያውቁ መሆኑን፣ የምግብ ማብሰያ ክፍሎቹ፣ የማብሰያ ቁሳቁሶችና ለምግብነት የተዘጋጁት የእህል ዘሮች አያያዝ ለተመጋቢው ጤና ደህንነት በሚታሰብ መልኩ እንዳልሆኑና ይህንንም ጤና ጥበቃው መ/ቤት ችላ ብሎት መቆየቱን ነው አስተያየት ሰጪዎች የጠቆሙት።
“በጤና ጥበቃ ስር ያሉት የጤና ጣቢያዎችና የበሽታ መከላከያ ተቋማት ከሆቴሎቹና ከምግብ ቤቶች ቀድመው መታሸግ የሚኖርባቸው ናቸው፣ ጤናን በተመለከተ ለመስክ ሥራ የሚወጡት ደንብ አስከባሪ ሠራተኞቻቸው የቢራ ጉቦ ሲቀርብላቸው የፅዳት ጉድለትና ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ምግብ የሚዘጋጁባቸውን ሆቴሎች፣ ግሮሰሪዎችና ምግብ ቤቶች አልፈው የሚሄዱና ለኃላፊነት ብቁ ያልሆኑ ናቸው” የሚሉ ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚደርስበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለዘመናት አሠራሩን ሊያሻሽል ባለመቻሉ ነው ለበሽታው መከሰት አንዱ ምክንያት የሚሉ በርካቶች መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል።
በዚሁ በምህጻረ ቃል አተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) በመባል የሚታወቀውና በቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ አሳሳቢ የሆነው በሽታ ወደ አስር ሺ የሚጠጉ ሰዎች የተጠቁ ሲሆን፣ በርካቶችም ሕክምና ያላገኙ ናቸው።



