በኃይማኖት ግጭት አንድ ሰው ሲሞት 16 ቆሰሉ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2000 ዓ.ም. March 11,2008)፦ በምዕራብ አርሲ ዞን ወርቃን ወረዳ ሃንሱ ጨቢ በሚባል ቦታ በተነሳ የኃይማኖት ግጭት አንድ ሰው ሲሞት 16 ሰዎች ቆሰሉ። አንድ የፖሊስ አባልም የጉዳቱ ሰለባ ሆኖአል።
ባለፈው እሁድ የካቲት 23 ቀን 2000 ዓ.ም. ከቀኑ በሰባት ሰዓት፤ በምዕራብ አርሲ ዞን ወርቃን ከተባለች ወረዳ ከስምንት ሰዓት የእግር መንገድ በኋላ በምትገኘው «ሃንሱ ጨቢ» ውስጥ በእስልምናና ፕሮቴሰታንት እምነት ተከታዮች መካከል በተነሳው ብጥብጥ አደጋው ሊደርስ መቻሉ ታውቋል።
በአካባቢው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እምነታቸውን በሚያካሂዱበት ሁለት ቤተክርስቲያናት ውስጥ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች እንደሆኑ የሚገመቱ ግለሰቦች መውጫ መግቢያውን ዘግተው ስለት ባለው ነገር በመማታትና ጥይት በመተኮስ ጉዳት ማድረሳቸው ታውቋል።
የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮቹ አደጋው ሲበረታባቸው ያሰሙትን ጩኸት አድምጠው ወደ አካባቢው በተቃረቡ ሁለት ፖሊሶች ላይ ተኩስ መከፈቱና በተኩሱም አንዱ ፖሊስ ሲወድቅ፤ በወደቀበት በስለት ሌላ ድብደባ እንደተፈፀመበት የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። ጭፍጨፋው በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈፀመ መሆኑንና ከቆሰሉት 16 ሰዎች መካከል ለአካል ጉዳት የተጋለጠ እንደሚገኝበትም ለማረጋገጥ ተችሏል።
አካባቢው ከከተማ የራቀ በመሆኑ ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል በአፋጣኝ ሊደርስ ያልቻለ ሲሆን፣ ድርጊቱን የተቃወሙ ሌሎች የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንድ ላይ ተባብረው ነገሩን ሊያረጋጉና ጉዳቱ ወደሌሎች ሳይዛመት ማስጣላቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ 10 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ 16ቱ ቁስለኞችም ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡
ወርቃን ወረዳ ከሻሸመኔ ከተማ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ አደጋው የተከሰተባት "ሃንሱ ጨቢ" የተባለችው አካባቢ ደግሞ ከወርቃን ወረዳ በእግር የስምንት ሰዓት መንገድ ያስኬዳል።
ሃንሱ ጨቢ ቡና የሚበቅልበት በመሆኗ ከተለያየ አካባቢ ለሥራ መጥተው እዛው እንደሚቀሩና አልፎ አልፎ የኃይማኖትና የቦታ ፀብ የሚነሳባት አካባቢ እንደሆነች አካባቢውን በቅርብ የሚያውቁ ገልፀው፣ እንዲህ ዓይነት ከባድ አደጋ ሲደርስ ግን የመጀመሪያ እንደሆነ ጠቁመዋል።



