ለአውሮፓ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ካውንስል የተጻፈ

Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 4 ቀን 2000 ዓ.ም. March 13,2008) "ሠላማዊ ትግል ብቸኛው አማራጭ ነው" ሲል ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶችን በመዘርዘር በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ቅንጅት (አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ) ፓርቲ ለአውሮፓ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ካውንስል በፃፈው ደብዳቤ አስታወቀ።

 

ፓርቲው የደብዳቤውን ጉዳይ "የፓርቲያችንን የሠላማዊ የትግል ስልት ይመለከታል" በሚል ያስቀመጠው ሲሆን፣ በፓርቲው እሳቤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋናው ተልዕኮ የመንግሥት ሥልጣንን በህዝብ ፈቃድና በህዝብ ምርጫ በሕግ ለተወነሰ ጊዜ ተረክቦ የተሻሉ በሚሉአቸው የፖሊሲ አማራጮች ሀገርን ማስተዳደር መሆኑን ገልጿል።

ይኸው ደብዳቤ ፓርቲው በምንም ዓይነት መንገድ በወንድማማቾች መሀከል ጦርነት እንዲካሄድ እንደማይፈልግና ወደ ትጥቅ ትግል የገቡት ሁሉ ከዚያ የወገን ሕይወትን ከሚያጠፋና ንብረትን ከሚያወድም ትግል ወደ ሠላማዊ ትግል የሚመለሱበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ አጥብቆ እንደሚያምን አክሎ ይገልጻል። ለዚህም እንደሚታገልና የህዝብ ፈቃድ ሆኖ ፓርቲው ሥልጣን ከያዘም በትጥቅ ትግል ላይ ላሉት ሁሉ ሙሉ ዋስትና ሰጥቶ ወደ ሠላማዊ ትግል እንዲገቡ ጥረት እንደሚያደርግ ይገልጻል።

ሠላማዊ ትግል ብቸኛው አማራጭ ነው ብሎ ፓርቲው የሚያምንበትን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ከዘረዘረ በኋላ፣ ፓርቲው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወደ ሥልጡን ፖለቲካ፣ ዜጎችን ወደ ነፃነትና ብልጽግና እራሱንም ወደ ላቀ ጥንካሬና ዲሞክራሲያዊነት ለማሳደግና ለማሸጋገር ብቸኛው መንገድ የሠላማዊ ትግል ብቻ መሆኑን እንደሚያምን ደግሞ እንደሚያረጋግጥ ይገልጻል።

በመጨረሻም ፓርቲው በቆመለትና በሚታገልለት ዓላማ ዙሪያ በመሰባሰብ ለሚደረገው ትግል የፓርቲው የድጋፍ ድርጅቶች የሚያደርጉትን የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የፋይናንስ እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፏል።

ደብዳቤው የተፈረመው በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሯ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ነው። (ሙሉውን ደብዳቤ አስነብበኝ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ