በትግራይ አውቶቡስ ላይ ፈንጅ ፈንድቶ 8 ሰዎች ሞቱ 22 ቆሰሉ
"የሻዕቢያ እጅ አለበት" የኢህአዴግ ባለሥልጣናት
Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 4 ቀን 2000 ዓ.ም. March 13,2008)፦ ከሁመራ ከተማ ወደ መቀሌ ይጓዝ የነበረ 60 ሰዎችን በጫነ ሰላም በመባል የሚታወቅ የህዝብ ማጓጓዣ አውቶቡስ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ፈንድቶ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ 22 ሰዎች መቁሰላቸውን ዛሬ አመሻሹ ላይ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።
በትናንትናው ዕለት ከሁመራ ከተማ 60 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ መቀሌ ለመጓዝ ጠዋት ከአውቶብስ መናኸሪያው ወጥቶ 60 ሜትር ያህል እንደሄደ ፍንዳታው ተከስቷል።
ፍንዳታው እንደተከሰት አውቶብሱ የተበታተነ መሆኑን የገለጹት የዓይን ምስክሮች እንዳረጋገጡት ከፍተኛ የሆነ፣ የፍንዳታ ድምፅ መሰማቱንና አካባቢውም መረበሹን ገልጸው፤ በተሳፋሪው ላይ የደረሰው ጉዳት አሰቃቂ እንደነበር ተናግረዋል።
እስከአሁን ምንም አይነት በምርመራ የተገኘ ውጤት ባይኖርም የሻዕቢያ እጅ አለበት ሲል የኢህአዴግ መንግሥት ባለሥልጣናት ክስ ማሰማት መጀመራቸው ታውቋል።
ቁስለኞች በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል ለእርዳታ እንደተወሰዱ ለማወቅ ከመቻላችንም በላይ ፈንጂው በሰዓት የተጠመደ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገልጿል።



