አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ለሦስተኛ ጊዜ ተቀጠረ
Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2000 ዓ.ም. March 14,2008)፦ የመስራች አባላት የፊርማ ማሰባሰቢያ ቅጽ እንዲሰጣቸው የጠየቁት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባላት ለሦስተኛ ጊዜ ለሰኞ መቀጠራቸው የምርጫ ቦርድ ሥርዓትን ያልተከተለ አሰራር ነው ሲሉ ታዛቢዎች አስተያየት ሰጡ።
አንድ ድርጅት ወይንም ቡድን የሚያቀርብለትን የፊርማ ማሰባሰቢያ ቅጽ መጠየቂያ ደብዳቤ በአፋጣኝ መመለስ የተለመደና ሕጋዊ አሰራር ቢሆንም፤ የምርጫ ቦርድ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ አባላት ጉዳዩን እንዲከታተሉ የመደቧቸውን አቶ ሙሉነህ ኢዩኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ያለምክንያት እያመላለሷቸው ከመሆኑም በላይ፣ የፓርቲዎች ምዝገባ ኃላፊ የሆኑት አቶ መኮንን ወንድሙ ሰኞ ጠቅላላ ውሳኔ እንሰጣችኋለን ሲሉ የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻ በሊቀመንበሯ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሁኔታውን በሚመለከት ሕጋዊ አሰራር የተከተለ አለመሆኑን ሲጠየቁ ‘ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔ ይሰጣችኋል’ ሲሉ መመለሳቸውን ውስጥ አዋቂዎች ተናግረዋል።
የአቶ ተስፋዬ ምላሽ አግባብ አይደለም የሚሉ ታዛቢዎች የፊርማ ማሰባሰቢያ ቅጽ ለመስጠት የቦርድ ስብሰባና ውሳኔ ድረስ የማያደርስ ከመሆኑም በላይ በመዝገብ ቤት የሚጠናቀቅ መሆኑን አስምረውበታል። እነዚሁ ታዛቢዎች "ይህ አይነት አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሰዎች ላይ የተከሰተ አስገራሚ ክስተት ነው" ብለዋል።



