ለወ/ት ብርቱካን ቤተሰቦች መርጃ በሲያትል የራት ምሽት ተዘጋጀ
ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርባል
Ethiopia Zare (ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን 2002 ዓ.ም. November 12, 2009)፦ ገቢው ሙሉ ለሙሉ በእስር ለምትገኘው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ቤተሰቦች መርጃ የሚሆን የራትና የሙዚቃ ምሽት በሲያትል አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ከሲያትል አንድነት ጋር በመተባበር ማዘጋጀታቸው ተገለጸ።
በዕድሜ ልክ እስራት ፍርድ ወደ እስር ቤት ተጥላ ለአንድ ዓመት ያህል በቃሊቲ እስር ቤት የምትገኘው ወጣት ሴት የፖለቲካ መሪ ወ/ት ብርቱካን ወላጅ እናቷን ጨምሮ የአምስት ዓመት ህጻን ልጅና ሌሎች ቤተሰቦቿን ታስተዳድር የነበረ መሆኑ ይታወቃል።
በሲያትል የተዘጋጀው ይሄው የወ/ት ብርቱካንን ቤተሰቦች መርጃ የራትና የሙዚቃ ዝግጅት በተለይ በከተማው የሚኖሩ ወጣት የመጀመሪያና የከፍተኛ ት/ቤት እንዲሁም የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ከሲያትል የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ማኅበር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
የራት ዝግጅቱ እሁድ ኖቨምበር 15 ከ5 - 9 PM በአሲምባ ሬስቶራንት የሚዘጋጅ ሲሆን፤ በሬስቶራንቱ አዳራሽ ምሽቱን ዝነኛው ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ለዚሁ ለወ/ት ብርቱካን ቤተሰቦች መርጃ የሚሆን የሙዚቃ ዝግጅት እንደሚያቀርብ ለመረዳት ችለናል።
በዝግጅቱ ላይ በፖርትላንድ እና በቫንኩቨር ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በዚህ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ምሽት እንደሚሳተፉ ታውቋል።
አድራሻ፦ Assimba Restaurant (MLK and Cherry st. Intersection)
ቀን እና ሰዓት፦ Sunday November 15, 2009 from 5 - 9 PM



