ፕ/ር ኤፍሬም ፖለቲከኞቹን ይቅር ሊያባብሉ ከላይ ታች እያሉ ነው
Ethiopia Zare (አርብ ኅዳር 4 ቀን 2002 ዓ.ም. November 13, 2009)፦ የቅንጅት እስረኞችን በማስፈታት ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል የሚባለው በፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራው የሽማግሌዎች ቡድን መድረክንና ኢህአዲግን ለመሸምገል ከታች ከላይ ማለት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
ፕሮፌሠሩ ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በሸራተን ሆቴል ለሁለት ቀን ከመድረክ አመራሮች በተለይ ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው፣ ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስን እና አቶ ገብሩ አስራትን አነጋግረዋል ሲሉ ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።
የማስታረቅ ሥራ ከጀመሩትም ውስጥ ስድስት የሽማግሌዎች ቡድን አባላት በስብሰባው ላይ ተሳትፈው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
የሽማግሌዎቹ ቡድን ውጥረቱ አሳሰቦኛል ዕለት ተዕለት ሁለቱ ፓርቲዎች እየተፋጠጡ መጥተዋል ይህ መቅረት አለበት ብለዋል። መድረኮች ውጥረቱን ያባባሰው ኢህአዲግ ነው፤ ባለው ሚዲያ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የከፈተው እሱ ነው፤ ማቆምም ያለበት ገዥው ፓርቲ እንጂ እኛ ምንም አይነት ጥፋት የለንም ማለታቸው ታውቋል።
መድረክ ከኢህአዲግ ጋር ብቻውን ለመወያየት የፈለገው ስለምርጫ ሥነ-ምግባር ሳይሆን ሌሎች ተደራዳሪዎች በአጀንዳነት ያልያዙት ለየት ያሉ አጀንዳዎች ስላለው ነው በማለትም ጥቅምት 29 ቀን ባወጣው መግለጫው መጥቀሱ ይታወቃል።