Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 11 ቀን 2000 ዓ.ም. March 20,2008) ኢህአዴግ በሚያዚያ ወር ለሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሟሟያ ምርጫና ለክፍለ ከተማ ምርጫ ስምንት የመንግሥት ጋዜጠኞችን ለፓርቲው በእጩነት ማቅረቡ ታወቀ።

 

እነዚህ በእጩነት የቀረቡት የመንግሥት ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ ከኢትዮጵያ ሬድዮና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው። ዝርዝራቸውን ከዚህ እንደሚከተለው ይገኛል።

1ኛ አቶ ፀጋዬ በየነ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ትግርኛ ክፍል፣

2ኛ አቶ አበበ ያረጋል የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ፣

3ኛ ወ/ት ብርቱካን ሐረገወይን የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋዜጠኛና በአሁኑ ሰዓት በውሰት የብሔራዊ ሚሊኒየም ጽ/ቤት ሠራተኛ፣

4ኛ አቶ ኪሮስ ገ/እግዚአብሔር - ከኢትዮጵያ ሬድዩ፣

5ኛ ወ/ሮ አልማዝ ካህሳይ - ከኢትዮጵያ ሬድዮ፣

6ኛ አቶ ጋሻው ተፈራ - ከኢትዮጵያ ሬድዮ፣

7ኛ ወ/ሮ አስናቀች ደምሴ - ከኢትዮጵያ ሬድዮ እና

8ኛ ወ/ት ታፈሱ አባይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞች መሆናቸው ታውቋል።

ይሄንን የኢህአዴግ እጩ ተወዳዳሪዎች አስመልክቶ አዲስ አበባ ያለው የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ካነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች አንድ አዛውንት "ኢህአዴግ እፍረት ያጣና ዓይን ያወጣ ፓርቲ ስለመሆኑ በተለይ ምርጫን አስመልክቶ የሚከተላቸውን መስመሮች መመልከቱ በቂ ነው፤ ይኸኛውም አንዱ ነው" ብለዋል።

ለነፃው ፕሬስ ቅርበት ካላቸው ወገኖች አንድ ግለሰብ ደግሞ "መንግሥት በተቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙኀን ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ዘጠና ከመቶው በላይ ቢያንስ የፓርቲው አባል መሆናቸው የተረጋገጠ ነው" በማለት አስተያየታቸውን ይጀምሩና "... ታዲያ እነዚህ ጋዜጠኞች ለፓርቲያቸው ዘብ መቆማቸውን ለማረጋገጥ ለፓርቲው በእጩነት ለምርጫ መቅረባቸው አያስደንቅም" ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ማሟያ ምርጫና የክፍለ ከተሞች ምርጫ በሚያዚያ ወር 2000 ዓ.ም. እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ