የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ በሙስና ሹም ሽር አደረጉ
Ethiopia Zare (ሰኞ ኅዳር 28 ቀን 2002 ዓ.ም. December 7, 2009)፦ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊና የከፋ ዞን የህዝብ እንደራሴ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አዴሎ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሙስና መፈጸማቸውን የከፋ ዞን ሠራተኞች ገለጹ።
ሠራተኞቹ ከጥቅምት 23 እስከ ኅዳር 2 በቦንጋ ከተማ ባደረጉት ስብስባ ሠራተኞችን አላግባብ ከሥራ እንዲፈናቀሉና ዘመዶቻቸውን በትዕዛዝ እንዲቀጠሩ አድርገዋል በማለት የጽ/ቤት ኃላፊውን በግምገማ አጋልጠዋል።
በስብሰባው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ለታዛቢነት የተላኩትን አቶ እምሩ ወይሳን በምክንያት ከፓርቲው እንዲባረሩ አድርገዋል ያሉት ሠራተኞች፤ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሠራተኞችን እንደፈለጉ የሚያደርጉና ለኃላፊነቱ ብቁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
አቶ ብርሃኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዋጅ በወጣበት ጊዜ አንደበታቸውን ሳይቆጣጠሩ ሰዎችን አልባሌ ንግግር በመናገር በአደባባይ ያጣጥሉ እንደነበር በስፍራው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል።
ኃላፊው ይህ ሁሉ ወቀሳና ግምገማ ቢቀርብባቸውም እስካሁን ከሥራ ኃላፊነታቸው እንዳልተነሱ ወይም እስካሁን በሚመጥናቸው የሥራ ድርሻ ሳይሰጣቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የማማከር ሥራቸውን እንደቀጠሉ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል።



