የኢሰመጉ አባላት ከሀገር እየተሰደዱ ነው
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. December 11, 2009)፦ ቀድሞ በፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም በኋላም በአቶ አበበ ወርቄ ይመራ የነበረውና በመያዶች (NGO) አዋጅ ምክንያት በመፍረስ ላይ ያለው የኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ) አባላት ከሀገር እየወጡ መሆኑ ተሠማ።
መንግሥት በክፉ ዓይን የሚያየው ይኸው ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በአዲሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕግ መሰረት መሥራት የማይችልበት ደረጃ ከመድረሱም በላይ፤ ያለውን ማናቸውንም ንብረቱንና ገንዘቡን ለመንግሥት እንዲያስረክብ መጠየቁን ውስጥ አዋቂዎች ምንጮች ገልጸዋል።
በቅርቡ ወደ ኬንያ የተሰደዱ የኢሰመጉ ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ እንዳለ የገለጹት ምንጮቻችን፤ ዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ኬንያ ለገቡት የኢሰመጉ ሠራተኞች ወጪዎቻቸውን ጨምሮ አጠቃላይ የደህንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዘጋቢዎች ጋዜጣቸው ከተዘጋ በኋላ ኬንያ ከገቡበት ዕለት ጀምሮ በዚሁ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አማካይነት ጥገኝነት አግኝተው የመጠለያ ወጪያቸው እንደተሸፈነላቸውና ወደ ተለያዩ ሦስተኛ ሀገራት እንዲሄዱም ሙከራ መጀመሩን ለማወቅ ችለናል።



