አቶ አየለ ጫሚሶና ፓርቲያቸው ጋዜጠኞችንና እነወ/ት ብርቱካንን ሊከሱ ይችላሉ
ምርጫ ቦርድ ተባባሪ ነው
Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 11 ቀን 2000 ዓ.ም. March 20,2008)፦ ምርጫ ቦርድ የቅንጅትን ሕጋዊ ሠርቲፊኬት በመስጠት እውቅና የሰጠውና በአቶ አየለ ጫሚሶ ሊቀመንበርነት የሚመራ ፓርቲ፤ ከአሁን በኋላ የቅንጅት የፓርቲ አባል ያልሆኑ ሰዎችን ስለቅንጅት የሚጠይቁ ጋዜጠኞችን እና የፓርቲያቸው አባል ሳይሆኑ በፓርቲው ስም መልስ የሚሰጡትን ግለሰቦች ለመክሰስ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለፁ።
ፓርቲው በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ እየታተሙ የሚወጡ ጋዜጦች ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞችና፣ በተለይ በወ/ት ብርቱካን እና በኢንጂነር ኃይሉ የሚመሩትን ፓርቲዎች አመራሮች እስካሁን ሲያደርጉ በነበሩትበት ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ ክስ እንደሚመሰርትባቸው ታውቋል።
እንደኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለፃ ከሆነ በኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአቶ አየለ ጫሚሶ ፓርቲ ጋር በመተባበር ፓርቲው በጋዜጠኞችና በግለሰቦቹ ላይ ክስ መመስረት የሚያስችለውን ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጽፎለታል።
አንዳንድ የሀገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች በዘገባዎቻቸው ላይ በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ፓርቲ ያልሆኑ ግለሰቦችን "የቀድሞ የቅንጅት አመራሮች"፣ "የቅንጅት አመራሮች"፣ "የቅንጅት ሊቀመንበር"፣ "የቅንጅት ተ/ም/ሊቀመንበር"፣ ... እያሉ ማስፈራቸው ይታወቃል። ከዚህም ሌላ ከምርጫው በፊት በቅንጅት ፓርቲ ስር አንድ ላይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች በቅንጅት ስም መግለጫ መስጠታቸው፣ ቃለምልልስ እንደሚያደርጉ ይታወቃል።
ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ወገኖች እንደገለፁት ከሆነ እነዚህ ጋዜጦችና ግለሰቦች ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ክሱ የሚመሰረተው በጋዜጦቹ የሚወጡት ዘገባዎች በህዝብ ውስጥ ውዥንብር ፈጥረዋል በሚል ይሆናል።
ምንጮቻችን በተለይ "ቅንጅት የስም ለውጥ አደረገ"፣ "ቅንጅት አንድነት ተባለ"፣ ... ተብሎ መዘገቡ በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራውን ፓርቲ አመራር አባላት በጣም እንዳበሳጫቸው ገልፀዋል።



