እነ ዳንኤልና ነፃነት ለመጋቢት 25 ተቀጠሩ
ዛሬ ፍርድ ቤቱ ተጨናንቆ ነበር
Ethiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. March 25,2008)፦ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በእነአቶ ዳንኤልና ነፃነት በኩልና በዓቃቢ ሕግ በኩል በተለያየ መልኩ ቀርቦለት ነበረውን የይግባኝ ጥያቄ በአንድ ላይ ለመጋቢት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. እንደሚያይ በስፍራው የተገኘ ዘጋቢያችን ገለጸ።
በፍርድ ቤቱ አካባቢ ችሎቱን ለመከታተል የእነ ዳንኤልና ነፃነትን ቤተሰቦች ጨምሮ በርካታ የተለያዩ የኢንባሲዎች ታዛቢዎች፣ የሃገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተዎካዮችና ከእስር የተፈቱ የቅንጅት ወይንም የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በስፍራው ተገኝተዋል። ብዛት ያለው ህዝብም ፍርድ ቤቱን አጨናንቆት እንደነበር ታውቋል።
የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ ዳንኤልና ነፃነት በኩል የቀረበለትን የዋስ መብትና በነፃ የመለቀቅ የይግባኝ ጥያቄ ለመጋቢት 16፤ በዓቃቢ ሕግ የቀረበለትን እንደ ቅንጅት አመራሮች ከዕድሜ ልክ እስከ ሞት የሚያስቀጣ የይግባኝ ጥያቄ ለመጋቢት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ቀጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ለአምስት ደቂቃ ተሰይሞ በዋለው ችሎት የሁለቱንም የይግባኝ ጥያቄ ለመጋቢት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. በአንድ ላይ የሚያይ መሆኑንና በእነ ዳንኤልና ነፃነት በኩል የቀረበውን ጥያቄ ጠበቃቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የፊታችን ዓርብ ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መውሰድ እንደሚችሉ በፍርድ ቤቱ መለጹን ለማወቅ ችለናል።
ሁኔታውን በሚመለከት በኖርዝ አሜሪካ ነዋሪነታቸውን ያረጉ ኢትዮጵያዊ የሕግ ባለሙያ አነጋግረን በሰጡን አስተያየት፤ አምባገነናዊ አገዛዝን ለመቃወም በተለይ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን ብቻ ለማስፈታት በሚደረግ ጥረት ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን በእንደዚህ ያሉ ቆራጥ የመብት ተሟጋቾችን ስም በማንሳት ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች በየሃገራቱ እስካሁን አለመጠራቱና ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ አለመቻሉ ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጸዋል።
እኚሁ ኢትዮጵያዊ የሕግ ባለሙያ "አሁንም ቢሆን ጊዜ ሳይሰጠው በውጭ የሚገኙ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው በመነሳት ለዓለም ማኅበረሰብ በማሳወቅ ለእነዚህ ወጣት ምሁራን አጋርነታቸውን ማሳየት አለባቸው" ሲሉ በቁጭት ገልውልናል።
አክለው እንደተናሩትም "የእነኝህ አንጡራ ሀብት ወጣቶችን ቤተሰቦች መንከባከብና በግፍ ለታሰሩት ወጣቶች ስንቅ የማቀበል ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል" ሲሉ አስምረውበታል።



