ዳንኤልና ነፃነት በሽምግልና ሊፈቱ ነው
Ethiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. March 25,2008)፦ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሞክረዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት የሆኑት አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴን ከእስር ለማስፈታት የሽምግልና ጥረት መጀመሩን አንድ ታማኝ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጭ ገለጸ።
አገር ቤት ከሚገኙ ምንጮቻችን አንዱ እንደገለጸው አቶ ዳንኤል እና አቶ ነፃነት በፍርድ ቤት ሲከራከሩ ቆይተው ሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስር የተፈረደባቸው ቢሆንም፤ በሕጉ መሰረት የእስራት ጊዜያቸውን ጨርሰው በአመክሮ መፈታት ሲገባቸው 'ፀባያቸው አልታረመም' በሚል እስካሁን በእስር ይገኛሉ።
በተጨማሪም የፌደራል ዓቃቤ ሕግ በእስር ላይ እያሉ ይግባኝ የጠየቀ በመሆኑ በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራው የአገር ሽማግሌዎች ሕብረት ሁለቱም ተከሳሾች ይቅርታ ጠይቀው ከእስር እንዲፈቱ ለማድረግ ጥረት መጀመራቸውን ይኸው ምንጫችን ገልጿል።
በትናትናው ዕለት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ ቃሊቲ እስር ቤት ተገኝተው እስር ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ተከሳሾች ያነጋገሩ ሲሆን፣ ከእስር ስለመፈታታቸው ተስፋ እንዳለው ለቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
ምንጫችን ምናልባትም የሽምግልና ሂደቱ ከዘጠኝ ቀን በኋላ የተቀጠረው ይግባኝ ከመድረሱ በፊት እንደሆነ ጠቁመዋል። ለዚህም እንደማስረጃ ሊሆን ይችላል በሚል ምንጫችን የገለጸው፤ በዛሬው ዕለት የነበረው የእነዳንኤል ይግባኝ ቀጠሮ ሲተላለፍ በቀጠሮው መቀየር ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ለተከሳሾቹ ከዳኞች ሲቀርብ "የተጀመረ ነገር ስላለና ለሱም ስለሚረዳን የቀጠሮው ቀን መቀየሩ ችግር አያመጣብን" በሚል መልስ ሰጥተዋል።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሌሎች ምንጮቻችንም የተጀመረው ነገር ሽምግልና መሆኑን ጠቁመዋል።



