የአሰቦት ጥንታዊ ገዳም በዚህን ሰዓት እየተቃጠለ ነው
Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 18 ቀን 2000 ዓ.ም. March 27,2008)፦ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውና ረጅም ዕድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት የአሰቦት ገዳም የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደርሶበት በዚህን ሰዓት እየተቃጠለ እንደሆነ ኢትዮጵያ ያሉ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጡ።
እስካሁን በገዳሙ ይዞታ ስር በሚገኝ የደን ሀብትና የእርሻ መሬት ላይ በእሳት ቃጠሎው ክፉኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከቦታው መረጃውን ያደረሱን ምንጮቻችን የአካባቢውን ነዋሪዎች በመጥቀስ እንደገለጹት፣ የሰደድ እሳቱ ትናንት ረቡዕ ጧት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከአንድ ሰዓት ጀምሮ እስካሁን ይህንን ዜና በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጹ ላይ እስካወጣንበት ድረስ ለመቆጣጠር አለመቻሉን ለማወቅ ችለናል።
የአካባቢው ህዝብ እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረበ እንደሆነ የገለጹት ምንጮቻችን፤ የመንግሥት የእሳት አደጋና መከላከያ በጊዜ ሊደርስ እንዳልቻለ ገልጸዋል። እስካሁን የአካባቢው ነዋሪዎችና ኅብረተሰብ በአቅራቢያው በተገኙ አይሱዙ መኪናዎች ውሃ በማመላለስ ለማጥፋት እየተሞከረ እንደሆነ አስረድተዋል።
በእሳት ቃጠሎው በገዳሙ የሚኖሩ መነኮሳት ቤቶች ሳይቃጠሉ እንዳልቀሩና የገዳሙን መቅደስ ሊነካው እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።
ይህን ዜና እስከተጠናከረበት ዛሬ ማምሻውን ድረስ እሳቱን መቆጣጠር ያልተቻለ ሲሆን፣ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰም ለመገመት አልተቻለም። የእሳቱ መንስኤ በድርቅ ምክንያት የተከሰተ ሰደድ እሳት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።



