Yedrasiw Mastawesha / የደራሲው ማስታወሻአዲሱ መጽሐፍ “የደራሲው ማስታወሻ” የተሰኘ ሲሆን፣ ቀጣዩ ደግሞ “የስደተኛው ማስታወሻ” ነው

Ethiopia Zare (እሁድ መጋቢት 19 ቀን 2002 ዓ.ም. March 28, 2010)፦ የደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ “የደራሲው ማስታወሻ” የተሰኘው አዲሱ መጽሐፍ የፊታችን ሚያዝያ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. (አፕሪል 10 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በገበያ ላይ እንደሚውል የመጽሐፉ አሳታሚ “ነፃነት አሣታሚና አከፋፋይ” ለኢትዮጵያ ዛሬ በላከው መልዕክት ገለጸ።

 

“የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተሰኘው መጽሐፍ ተከታይ የሆነውና “የደራሲው ማስታወሻ” የተሰኘው ይኸው መጽሐፍ 424 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በቅርቡ በዓለም ላይ በሚገኙ የኢትዮጵያውያን ሱቆች፣ ምግብ ቤቶችና የተለያዩ ቦታዎች በገበያ ላይ እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል።

 

በመጽሐፉ መግቢያ ላይ “... በኔ በኩል የጋዜጠኛነት ግዴታዬን እየተወጣሁ ነው። የዓይን ምስክሮች የገለፁልኝን ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት አለብኝ ብዬ አምናለሁ። ወደፊትም የሙያው ሥነምግባር በሚፈቅድልኝ ደረጃ እገፋበታለሁ። ጓደኞቼ ሆይ! ገና ብዙ እፅፋለሁ!! “ምናገባኝ” ወይም “ጎመን በጤና” ብዬ የምተወው ጉዳይ የለም። የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል። “ጎመን በጤና” የሚለው ዘፈንም የማደንዘዣ መርፌ ነው። እኛ ከክብርና ከኩራታችን ጋር የተፈጠርን ሙሉ ሰዎች ነን። በመሆኑም እንደ ሐበሻ ውሻ ሳይሆን እንደ ሐበሻ ሰው ለመኖርና ለመሞት እንመጥናለን። ...” ይላል ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ።

 

ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ በዚህ አዲሱ መጽሐፉ በተለይም በሥልጣን ላይ የሚገኙትንና ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉትንና ቀድሞ በሥልጣን ላይ የነበሩትን ግለሰቦች ስብዕና የበለጠ አጉልቶ እንዳሳየበት ለመረዳት ተችሏል። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ አቶ በረከት ስምዖን፣ ጄኔራል ሣሞራ የኑስ፣ አቶ ዳዊት ዮሐንስ፣ ጄኔራል አባዱላ ገመዳ፣ ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሣዔ፣ አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ ስየ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ ታምራት ላይኔ፣ አቶ ክንፈ ገ/መድኅን፣ ... በርካቶች በሥርዓቱና በድርጅቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸውን ሰዎች ስብዕና በ“የደራሲው ማስታወሻ” ውስጥ መካተታቸው ታውቋል።

 

አሣታሚ ድርጅቱ በ“የደራሲው ማስታወሻ” ከተጠቀሱ ስሞችና ከተዳሰሱ ጉዳዮች ውስጥ ዋለልኝ መኮንንና ማርታ አሟሟታቸው ብቻ ሳይሆን ማን ተኩሶ እንደገደላቸው መጠቆሙን ገልጿል። አስመሮም ለገሰና የገዳ ሥርዓት፤ የሙሉጌታ አለምሰገድና የሲ.አይ.ኤ. ግንኙነት፤ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና አቶ በረከት ስምዖን (በስብሰባ ላይ)፤ አቶ ተፈራ ዋልዋ እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ አቶ ታምራት ላይኔ በጭፈራ ዘመን፤ የአቶ ክንፈ ገብረመድኅን የመጠጥ ቤት ድብድብ፤ አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ እና ጄኔራል ታደሰ ብሩ፤ አህመድ ግራኝ እና አቶ በረከት ስምዖን፣ አርቲስት አለማየሁ እሸቴ እና አርቲስት ንዋይ ደበበ፤ ... በመጽሐፉ ተጠቅሰዋል። ተዳስሰዋል። በጨረፍታም ቢሆን ስማቸው ተነስቷል።

 

የደራሲው ማስታወሻ እንደ ቀድሞው የጋዜጠኛው ማስታወሻ መጽሐፍ በሥነግጥም የታጀበ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። የገጣሚያን ደበበ ሰይፉ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ አሌክሳንደር ፑሽኪን፣ ስብኃት ገብረእግዚአብሔር፣ ታገል ሰይፉ፣ አበራ ለማ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ... ግጥሞች በመጽሐፉ ውስጥ ሥፍራ ተሰጥቷቸዋል።

 

መጽሐፉ የሀገሪቱን ባለሥልጣናት ስብዕና፣ ምርጫ 97ን፣ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት፣ ... እና ሌሎች ደረቅ ፖለቲካዎች ብቻ የታጨቁበት ሳይሆን በርካታ አዝናኝና አስቂኝ እንዲሁም የፍቅር ታሪኮች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል። ሳይጠቀሱ ከማያልፉት ታሪኮች ውስጥ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን የአቶ ስዩም መስፍንን አስደናቂና አስገራሚ የጋብቻዎች ታሪኮችን ጨምሮ ማካተቱ ታውቋል።

 

ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ ከነፃነት አሳታሚና አከፋፋይ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ላይ ይህንን መጽሐፍ የሚያሳትምለትና የሚያከፋፍልለት ሁነኛ አሳታሚና አከፋፋይ አጥቶ እንደነበር የገለጸ ሲሆን፤ መጽሐፉን በስምንት ወራት ውስጥ ጽፎ እንደጨረሰው ገልጿል። ቀጣዩንና መጻፍ የጀመረውን መጽሐፉን ደግሞ “የስደተኛው ማስታወሻ” የሚል ርዕስ እንደሰጠው ገልጿል።

 

“የደራሲው ማስታወሻ” የተሰኘውን አዲሱን መጽሐፍ ከወዲሁ በኢንተርኔት ማዘዝ እንደሚቻልና ዋጋውም 20 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ነፃነት አሳታሚና አከፋፋይ አስታውቋል። (መጽሐፉን ለማዘዝ ለምትፈልጉ “http://www.npabooks.com ”ን መጎብኘት ትችላላችሁ።)

 

ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ የደርግ ወታደር ሆኖ ሲዋጋ በወያኔ/ኢህአዲግ ተማርኮ፤ ከኢህአዲግ ጋር አዲስ አበባ የገባና፣ በኋላም በማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ፣ የ“እፎይታ” ጋዜጣና መጽሔት አሳታሚና ዋና አዘጋጅ ሆኖ አገልግሏል። በመጨረሻም ለስደት ተዳርጎ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ እንደሚገኝ ይታወቃል። በደቡብ አፍሪካም እያለ "የጋዜጠኛው ማስታወሻ" የተሰኘውን መጽሐፍ መጻፉ ይታወቃል።

 

በጋዜጠኝነት ሙያ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው ተስፋዬ ገብረአብ 41 ዓመቱ ሲሆን ተወልዶ ያደገው በደብረዘይት ነው። “ያልተመለሰው ባቡር”፣ “የቡርቃ ዝምታ”፣ እና “የቢሾፍቱ ቆሪጦች” የተባሉ ሦስት ልብወለድ መጻሕፍትን መጻፉ ይታወቃል። “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” እና “እፍታ” የተሰኙትን ቅጾች ያዘጋጅ የነበረ ሲሆን፣ በእነዚህ ቅጾች ውስጥ በርካታ አጫጭር ልብወለዶች፣ ግለታሪኮች እና መጣጥፎችን አቅርቧል። (ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ ከነፃነት አሳታሚና አከፋፋይ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ አስነብበኝ!)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ