Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2002 ዓ.ም. April 7, 2010)፦ የስምንት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መድረክ፤ በመናገሻዋ አዲስ አበባ ከሚያደርጋቸው ህዝባዊ ውይይቶች በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሁድ ሚያዝያ 2 እና 3 ቀን 2002 ዓ.ም. በኢሊባቡር፣ መቱና በምዕራብ ሸዋ ወልቂጤ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ ገለጸ።

 

መድረክ በሁለቱ ቀናት በሚያደርገው ህዝባዊ ስብሰባ በሥፍራው ድርጅቱን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ያስተዋውቃል፣ የመድረኩን ዓላማና የወደፊት ተግባራት ግልጽ ከማድረጉም በተጨማሪ ከኅብረተሰቡ የሚቀርብለትን መሠረታዊና ወቅታዊነት ያላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንም የድርጅቱ የመቱና የምዕራብ ሸዋ አደራጆች መግለጻቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመድረክ ልዑካን ቡድን በአሜሪካ ለሚያደርጉት የ15 ቀናት ቆይታ ዛሬ መጋቢት 29 ቀን 2002 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ እንደሚነሱ ታውቋል። አቶ ገብሩ አሥራትን፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን እና ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራውን የሚያካትተው የመድረክ ልዑካን ቡድን በዋሽንግተን ዲሲ ከአሜሪካ ባለሥልጣኖች ጋር በኢትዮጵያ መፃዒ የፖለቲካ ዕድል እና በምርጫ 2002 “ፍትሐዊነት” ጉዳይ ዙሪያ ይነጋገራል ተብሏል።

 

መድረክ አሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያኖችና ደጋፊዎቹ ጋር ሰፊ ውይይቶችን የሚያደርግ ሲሆን፤ በሲያትል፣ በካሊፎርኒያ እና በዋሽንግተን ዲሲ የሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎች ቅድመ ሁኔታ መጠናቀቃቸውን ለመረዳት ተችሏል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ