Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 13 ቀን 2002 ዓ.ም. April 21, 2010)፦ በምክትል ሊቀመንበሩ ኢንጂንየር ግዛቸው የሚመራው አንድነት ”የፓርቲ አፍራሾች” ባላቸው በእነ ፕሮፌሠር መስፍን ላይ መግለጫ አወጣ።

 

የአንድነት-መድረክን ጠንካራ የምርጫ ዘመቻ ለማደናቀፍና ለማዳከም የሚካሄደውን የተቀነባበረ ሤራ ለማክሸፍና የድርጅቱን ሕልውና ለማረጋገጥ ለሚደረገው ትግል የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ እንዲቆም በምክትል ሊቀመንበር ኢንጂንየር ግዛቸው የሚመራው አንድነት ጥሪውን አቅርቧል።

 

ጥሪውን ያቀረበው አንድነት “ሕጋዊ ፓርቲን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማሰናከል የሚደረገው ርብርብ ይቁም!!” በሚል ርዕስ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሚያዝያ 8 ቀን 2002 ዓ.ም. ከረፈዱ 5 ሰዓት በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ ላይ፤ “ዝም አንልም” በሚል ስም እነ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምን ይዘው ከፓርቲው ”በሥርዓት ግድፈት” በሚል የተባረሩ የፓርቲው መሥራቾች እሁድ ሚያዝያ 10 ቀን 2002 ዓ.ም. የጠሩትን ስብሰባ ሕገ-ወጥ ነው ሲል በጥብቅ አውግዟል።

 

“የፓርቲውን መርኅና ደንብ የጣሱ አባላት ከተከታታይ ማስጠንቀቂያ በኋላ በአንድነት ደንብ መሠረት የተሰናበቱ ናቸው” የሚለው መግለጫ አክሎም፤ ”እየታየ ያለው ሁኔታ እነ “ዝም አንልም” በፓርቲው ላይ ኹከት ሲፈጥሩ፣ ሥራ ሲያደናቅፉ፣ ፓርቲው ሕልውና እንዳይኖረው ሲጥሩ እና የተለያዩ የመንግሥት አካላትም የእጅ አዙር ድጋፍ ሲሰጧቸው ነው” ብሏል።

 

ይኸው የአንድነት-መድረክ መግለጫ አያይዞ፤ “የምርጫውን ውድድር በንፁህ የጨዋታ ሕግ ማሸነፍ ያልለመደበት ኢህአዲግ ተቀናቃኞቹን በቆረጣ የማሸነፍ ፖሊሲው አንድ ስልት አድርጎ” የእነ “ዝም አንልምን” አፍራሽ እንቅስቃሴ ቢጠቀምበት አይገርምም” ብሏል።

 

የአንድነትን ፓርቲ አፍራሾች ኢህአዲግ ከሙሉ ዝግጅታቸው ጋር ቢያሰማራቸው የሚደንቅ እንደማይሆንም አንድነት በመግለጫው ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል። የአንድነት ፓርቲን ወቅታዊነት ያለው መግለጫ የሰጡት ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ አቶ አስራት ጣሴና አቶ አንዷለም አራጌ ሲሆኑ፤ የቀድሞ የአንድነት አባሎች በኮኮበ ፅባህ ት/ቤት የጠሩት ጠቅላላ ጉባዔ፤ ሕገ-ወጥ መሆኑን በማስመልከት ለአዲስ አበባ መስተዳደርና ለሚመለከታቸው ክፍሎች መጋቢት 29 ቀን 2002 ዓ.ም. ደብዳቤ የፃፉ መሆናቸውንም አሳውቀዋል።

 

ባሳለፍነው ሣምንት ”መርኅ ይከበር!” በሚል ስያሜ ይንቀሳቀሱ የነበሩት የአንድነት አባላት ጊዜያዊ ምርጫ አድርገው አመራሮችን የመረጡ ሲሆን፤ ፕሮፌሠር መስፍንን ወ/ት ብርቱካን እስክትፈታ ሥልጣን ጠባቂ በማድረግ በምክትል ሊቀመንበርነት መርጧል።

 

ፕ/ር መስፍን፤ ”ስሙ በአንድነት ይቀጥላል ወይስ አዲስ ስያሜ አለው?” ተብለው ሲጠየቁ፤ ብዛት ያለው የድርጅቱ አባላትን ያሰባሰቡ እንደመሆናቸው ስም እንደማይቀይሩና መሪያቸው ወ/ት ብርቱካን እስክትፈታና ፍትሃዊ እንቅስቃሴ እስከሚያደርጉ በአንድነት ስም ትግላችውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ