”የአንድነትን ሕልውና የመታደግ ጥረታችንን ሕገወጥነት አይገታውም” እነፕ/ር መስፍን
እነኢ/ር ግዛቸው የፓርቲውን የምስክር ወረቀት፣ ጽ/ቤቱን፣ ማሕተሙን፣ ሰነዶችና ንብረቶች እንዲያስረክቡ ተጠየቁ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2002 ዓ.ም. April 27, 2010)፦ እነፕ/ር መስፍን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን (አንድነትን) ሕጋዊነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት፣ ጽሕፈት ቤቱን፣ ማሕተሙን፣ ሰነዶችና ንብረቶችን እንዲያስረክቧቸው፤ ማሕተሙን እንዳይጠቀሙና እንቅስቃሴአቸውን እንዲያቆሙ ትናንት ለኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው የፃፉላቸውን ደብዳቤ አልቀበልም ማለታቸውን አስመልክቶ፤ በዛሬው ዕለት ”የአንድነትን ሕልውና የመታደግ ጥረታችንን ሕገወጥነት አይገታውም” በሚል መግለጫ አወጡ።
ባለፈው ሚያዝያ 10 ቀን 2002 ዓ.ም. ”መርኅ ይከበር!” የሚሉትና የአንድነት ፓርቲ መሥራቾች በአዲስ አበባ በኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ”ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ” በማድረግ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ መንቀሳቀስ መጀመሩ ታውቋል። (ጉባዔው ያሳለፈውን ባለአስር የአቋም መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)። ኢ/ር ግዛቸው የሚመሩት አንድነት/መድረክ በበኩሉ ”የፓርቲ አፍራሽ” እያለ በሚጠራቸው በእነፕ/ር መስፍን ላይ ባለፈው ሣምንት መግለጫ ማውጣቱን መዘገባችን አይዘነጋም።
ይኸው በፕ/ር መስፍን የሚመራው ቡድን ”ርክክብ እንዲፈፀም ስለመጠየቅ” በሚል በቀጥታ ለኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በአንድ ሦስተኛው አባላት በተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አለመገኘታቸውን ይጠቅስና ጉባዔው የደንብ ማሻሻል አድርጎ አዲስ የምክር ቤት አባላት መምረጡን ይገልጻል።
በመጨረሻም ”... አረካካቢ ኮሚቴ በማቋቋም፤ የፓርቲውን ሕጋዊነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት፣ ማሕተም፣ ጽሕፈት ቤት፣ ሰነዶችና ንብረቶች ርክክብ በመፈፀም የጉባዔውን ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ እያሳሰብን፤ ከዚህ ቀን ጀምሮ በፓርቲው ማሕተም በመጠቀም፣ የምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የፓርቲውን ደንብና የሀገሪቱን ሕግ የሚጻረር እንዲሁም የጉባዔውን ውሳኔ የሚጥስ መሆኑን እናስታውቃለን ...” ይላል፤ የእነፕ/ር መስፍን ደብዳቤ። (ሚያዝያ 18 ቀን 2002 ዓ.ም. ለኢ/ር ግዛቸው ሺፈራው የተፃፈውን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
ይኸው ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የአንድነት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ለሚገኝበት ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ”እንዲያውቁት” በሚል እንዲደርሳቸው መደረጉ ታውቋል። ከዚህም ሌላ ምርጫ ቦርዱ የጉባዔውን ውሳኔና ተያያዥ ሰነዶችን በሸኚ ደብዳቤ መላኩን ለመረዳት ተችሏል።
ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን እነፕ/ር መስፍን ባወጡት ”የአንድነትን ሕልውና የመታደግ ጥረታችንን ሕገወጥነት አይገታውም” በሚል ባወጡት መግለጫ፤ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የተላከላቸውን ደብዳቤ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውንና የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞችም እንዳይቀበሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ብለዋል። (የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች እንደወረደ አቅርበነዋል።)
የአንድነትን ሕልውና የመታደግ ጥረታችንን ሕገ ወጥነት አይገታውም
ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
ሚያዚያ 10 ቀን 2002 ዓ.ም. የተካሄደው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ በፓርቲው ህልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ መርምሮ ፓርቲው ዓላማው ተጠብቆና መርሆቹ ተከብረው መቀጠል የሚያስችለውን ውሳኔ አሳልፏል።
የፓርቲውን ሕልውና ለአደጋ አጋልጧል ያለውን አመራር ለውጧል፤ ለሕገ ወጥ አሰራር ምቹ ሁኔታ ፈጥረው የተገኙ የደንብ አንቀፆች እንዲሻሻሉና የመዋቅር ለውጥ እንዲደረግ ወስኗል።
በጠቅላላ ጉባዔው የተመረጠው አመራር የጉባኤውን ውሳኔ ሕጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለማስፈፀም በጀመረው እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መቅረብ ያለባቸውን ሰነዶች በሸኝ ደብዳቤ የላከ ሲሆን፤ የአንድነት ፅ/ቤት ለሚገኝበት የቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ የፓርቲው ንብረትና ሰነዶች ርክክብ ሕጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን እንዲከታተል የፃፈውን ደብዳቤ ሁለቱም አካላት የተቀበሉ ሲሆን፤ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ግን የተጻፈላቸውን ደብዳቤ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የፅ/ቤት ሠራተኞችም እንዳይቀበሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ደብዳቤ አልቀበልም በማለት የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ ተፈፃሚ እንዳይሆን ማድረግ አይቻልም፤ ከሕግ በላይ መሆንም አይቻልም።
በመሆኑም የፓርቲያችን የመጨረሻ የሥልጣን አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ የፓርቲያችንን ሕግ ባከበረና የአንድ ፓርቲ ሰዎች ሊፈፅሙት በሚገባ አግባብ እንዲከናወን ጥረታችን ይቀጥላል።
የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች፤ የሠላምና የዲሞክራሲ ወዳጆች እንዲሁም ለሕግ የበላይነት መከበር የቆሙ ኃይሎች ሁሉ የጥረታችን አጋዥ እንዲሆኑ እንጠይቃለን።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ሚያዚያ 19 ቀን 2002 ዓ.ም.
አዲስ አበባ



