በማትያስ ከተማ

  • ሞና ሳሊን ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ጠየቁ
  • የኢትዮጵያን መንግሥት ሥርዓት የለሽነት አጋለጡ

May day 2010, Stockholm, Sweden

Ethiopia Zare (ሰኞ ሚያዝያ 25 ቀን 2002 ዓ.ም. May 3, 2010)፦ ባለፈው ቅዳሜ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የዓለም ወዛደሮች ቀን (ሜይ ዴይ) በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ ዋለ። በዚህ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲና የሠራተኛው ማኅበር ባዘጋጁት በዓል ላይ ብዙ ሺህ ህዝብ የተገኘ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያንም የሰልፉ ተካፋይ ነበሩ።

 

ሰልፈኛው በ13፡00 ሰዓት (ከቀኑ በ7 ሰዓት) በሁመልጎርደን አደባባይ በመገናኘት ሰልፉን የጀመረ ሲሆን፣ ከ150 ያላነሱ የስዊድን ነዋሪዎችና ከዴንማርክ የመጡ ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጽሑፎችን በማንገብ ከሰልፈኛው ጋር ተቀላቅለው ወደ ባኖራባንቶርየት አደባባይ አምርተዋል።

 

 

May day 2010, Stockholm, Sweden
 

 

ከያዙት መፈክሮችና በድምፅ ካሰሟቸው መካከል፤ ”ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ!”፣ ”በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና የዲሞክራሲ መብት ይከበር!”፣ ”ነፃ ምርጫ ይኑር!”፣ ”የሕግ የበላይነትና የፕሬስ ነፃነት ይጠበቅ!”፣ ... የሚሉ ይገኙበታል።

 

በአደባባዩም ለሰልፈኛው ንግግር ያደረጉት ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው፣ በተደጋጋሚ ሀገሪቱን የመራውና በአሁኑ ሰዓት ተቃዋሚ የሆነው የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ መሪ የሆኑት ሞና ሳሊን እና የፓርቲው የስቶክሆልም ከንቲባ ካሪን የምቲን ናቸው።

 

ሞና ሳሊን በአፍሪካን ቀንድ አሁንም ተደጋጋሚ ችግር እንዳለ ገልጸው፤ በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና የተበላሸ እንደሆነ፣ ሕግና ሰብዓዊ መብትም እንደማይከበር ገልጸዋል።

 

አያይዘውም በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛ የሴት መሪ የሆኑት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እዚህ መጥተው ካነጋገሯቸው በኋላ ሕግን በጣሰ ሁኔታ መታሰራቸው እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው፤ እኚህ ለሕግና ለዲሞክራሲ መብት መከበር የቆሙ መሪ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ሞና ሳሊን በሚቀጥለው ብሔራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው አሸናፊ ከሆነ የሀገሪቱ መሪና ጠ/ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይታወቃል።

 

May day 2010, Stockholm, Sweden

 

በዚህ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያውያኑ ሊገኙ የቻሉት የኢትዮጵያውያን ሶሻል ዲሞክራቲክ ማኅበር እና የስዊድን የአንድነት ድጋፍ ማኅበር አስተባባሪነት ሲሆን፤ ሰልፉ ከተጠናቀቀ በኋላ ከአንድ መቶ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን የድጋፍ ማኅበሩ ባደረገው ልዩ ዝግጅት ላይ ተሰባስበው አምሽተዋል።

 

በዚሁ ምሽት ታዋቂ ግለሰቦች በቦታው የተገኙ ሲሆን፣ የፖለቲካ ሰዎች ንግግር አድርገዋል። ከዚህም ሌላ ወ/ሪት መስከረም (ማራኪ) እና አቶ ታጠቅ ተስፋዬ ግጥሞቻቸውን አቅርበዋል።

 

በተጨማሪ ከዴንማርክ ለሰልፉ ለመጡ አባላት የራት ግብዣ የተደረገ ሲሆን፣ ለመጓጓዣ የሚሆንም ገንዘብ በአቶ ሙሉጌታ በኃይሉ አስተባበሪነት ተሰብስቧል። ሆኖም እንግዶቹ በተሰጣቸው ገንዘብ ላይ ተጨማሪ ብር በማከል ገንዘቡ ለወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ቤተሰብ መርጃ እንዲሆን በአደራ ሰጥተዋል።

 

በዚህ በስዊድን የወዛደሮች ቀን ክብረ በዓል ላይ ኢትዮጵያውያን ሰልፈኞች በሕብረት ተገኝተው ሲሳተፉ የአሁን ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ