ሕብረቱ በምርጫው እንደማይሳተፍ ገለጸ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2000 ዓ.ም. April 5,2008)፦ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራውና ፓርላማ ገብቶ የሚንቀሳቀሰው ሕብረት በቅርቡ በሚካሄደው የቀበሌ ምርጫ እንደማይሳተፍ አስታወቀ።
ሊቀመንበሩ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ትናንት በሰጡት መግለጫ የኢህአዴግ መንግሥት በየክፍለ ሀገራቱ የሚገኙ ተመራጮቻቸው ላይ የሚያደርጉትን ወከባ መቋቋም እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ በምርጫው ላለመሳተፍ ምክንያት እንደሆናቸው ለማወቅ ተችሏል።
ፕ/ር በየነ በተቀዋሚነት ከተሰማሩበት ጊዜ ጀምሮ ምርጫው ተጭበርብሯል፣ የምርጫ ሳጥኖች ተሰርቀዋል፣ ... በማለት በየጊዜው አቤቱታ ቢያሰሙም በምርጫው ተሳትፈው ወደ ፓርላማም በመግባት ተቃውሟቸውን የሚቀጥሉ ቢሆንም፤ ትላንትና ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ አንሳተፍም ማለታቸው ተደምጧል።
ኢህአዴግ ለብቻው ለመወዳደር ብዛት ያላቸው ተመራጮቹን በማሰማራትና በአንድ ቀበሌ ሦስት መቶ የምክር ቤት አባላትን መመደብ ሆን ተብሎ መልቲ ፓርቲ ሲስተም በሀገሪቱ እንዳያብብ አገዛዙ ያወጣው ተንኮል መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አንድ መቶ ቀበሌዎች መኖራቸው ይታወቃል።



