አቡነ ጳውሎስ ስለሐውልታቸውና ፖስተሮች ጉዳይ ነገ ምላሽ እሰጣለሁ አሉ

Ethiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2003 ዓ.ም. October 25, 2010)፦ ባለፈው ሣምንት ዓርብ በአዲስ አበባ የተጀመረውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባዔ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኗ ችግሮች ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ በተለይ በአቡነ ሳሙኤልና በአቡነ ጳውሎስ ሐውልት ማሰራት ጉዳይ ላይ ሰፊ ክርክሮች እየተደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

 

ለጥቅምት ጠቅላላ ጉባዔ የተቀመጠው ሲኖዶስ፣ አቡነ ጳውሎስ ባሰሙት ንግግር የተጀመረ ሲሆን፤ የፓትርያርኩን በወቀሳ የታጀበ ንግግር በርካታ የሲኖዶሱ አባላት የተቃወሙት ከመሆኑም በላይ በጉባዔው ላይ በመነሳት የተቃውሞ ሃሳብ ሰጥተውበታል።

 

በተለይ አቡነ ጳውሎስ ያሠሯቸውን ሐውልት በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡበትና ድርጊቱም ሕገ ቀኖናን የሚጻረርና የአባቶችን ሥርዓት ያልተከተለ ሥራ መሆኑን መጻሕፍትን በማጣቀስ የተቃውሞ ሃሳብ የተሰጠበት ሲሆን፣ አቡነ ጳውሎስ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ነገ ምላሽ ልስጥበት በማለት እንዳለፉት ለማወቅ ተችሏል።

 

በጉባዔው በርካታ ሃሳቦች ተነስተው ለውሳኔና ለውይይት ቀርበዋል። ሲኖዶሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጨ አድርሰዋል በተባለው ምዝበራ ተጠያቂ እንዲሆኑና ከሥራ ገበታቸው እንዲነሱም ውሳኔ አስተላልፏል።

 

ሌላውና አከራካሪ ከሆኑት ጉዳዮች ዋንኛው የአቡነ ሳሙኤል ጉዳይ ውሳኔ ያላገኘ ሲሆን፣ ከበጀት ውጭ ገንዘብ አባክነዋል በሚሉና ዘርዘር ብለው በፓትሪያርኩ በኩል ለቀረበባቸው ውንጀላዎች ምላሽ ሰጥተው ሲኖዶሱ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

 

ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዲመለሱ የሚወተወትላቸውና በብዙኀን ምዕመናንና አባቶች ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፉት አቡነ ሳሙኤል ለፀሎት ከነበሩበት እየሩሳሌም ሲመለሱ ስማቸውን የሚያጎድፉ ጽሑፎች በቤተ ክህነት ዙሪያ ሲሰራጩ እንደነበር ይታወሳል።

 

አቡነ ሳሙኤልና ሌሎች ትጉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለአባ ጳውሎስ የሚወጡ አላስፈላጊ ወጭዎችንና የቤተ ክርስቲያኗን ሕግ ያልተከተለ የሥልጣን ድልድል በመቃወማቸው ከሥራ ድርሻቸው ከመቀየርና ከመባረር አልፎ ሌሊት ቤታቸው ድረስ በገቡና ባልታወቁ ግለሰቦች ማስፈራራትና ድብደባ ደርሶባቸው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ