የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስረኞች ኮሚቴ ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ
የካናዳ ባለስልጣናትና ኢትዮጵያዊ ምሁራን ንግግር ያደርጋሉ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2003 ዓ.ም. January 10, 2011)፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ (ኢፖእአኮ) በካናዳዋ መናገሻ ኦታዋ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ከህዝብ ጋር ለመወያየት የካናዳ ፓርላማ ተወካይ ሚስተር ፖል ዲዋርንና የፒስ ቢልድ ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ሎረድን ጨምሮ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ፕሮፌሰሮችን በመጋበዝ ህዝባዊ ስብሰባ መጥራቱ ተገለጸ።
ውይይቱ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ በተካተቱ የምሁራኑ ጽሁፎችን የተንተራሰ ከመሆኑም በላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይም ማብራሪያ እንደሚሰጥ ታውቋል።ሚስተር ዴቪድ ‘ሰላም በኢትዮጵያና በአፍሪካ’ በሚል ርእስ ጥናት የሚያቀርቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲዳብር ካናዳ ምን ማድረግ አለባት በሚል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የካናዳው ፓርላማ ተመራጭ ሚስተር ፖል ዲዋር ንግግት ያደርጋሉ።
በመቀጠልም በስብሰባው ላይ ንግግር ከሚያደርጉት ኢትዮጵያዊያን ምሁራን መካከል ዶከተር ቡሻ ታዓ የዩኒቬርሲቲ መምህርና የቀድሞ የቶሮነቶ የኢትዮጵያ ማሕበር ፕሬዝዳንት “ወደፊት ለመራመድ ያለፈውን መመልከት፤ የ20 ዓመቱ የጎጥ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የሚያስትለው መዘዝ”። በሚል ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን በኒው ዮርክ ሲቲ ዩኒቬርሲቲ የትምህርት ጉዳዮች ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ገላውዲዮስ አርአያ ደግሞ“በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረገው የዲሞክራሲ ግንባታ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ሕብረተሰብ አስተዋጽኦና ሚና” ዙሪያ ትንተና ይሰጣሉ።
በተጨማሪም በዶውሰን ኮሌጅ የኢኮኖሚ ክፍለ ትምህርት ዋና ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ወርቁ አበራ የሚያቀርቡት ርዕስ “ያልተስተካከለ የጤና አገልግሎት በኢትዮጵያ” እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል።
ስብሰባው ቅዳሜ ጃንዋሪ 15 ቀን 2011 ከቀኑ 3 pm የሚጀምር ሲሆን ቦታው Bronson Centre, 211 Bronson Ave. እንደሚሆንና በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ዶክተር ገላውዴዎ “መንከባከብና ማስወገድ ያሉብን ባህሎች” በሚል ርእስ አዲስ በአማርኛ ያሳተሙትን መጽሃፍ እንደሚያቀርቡ ታውቋል።ሶሴፕ (ኢፖእአኮ) በመባል የሚታወቀው ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በተለያዩ ጊዜያት መግለጫዎችን በማውጣትና ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር ጥረት የሚያደርግ አካል መሆኑ ይታወቃል።



