Ethiopia Zare ረቡዕ የካቲት  9 ቀን 2003 .. Feb 17, 2011) በኦጋዴን አካባቢ የሚደረገው የአማጽያን እንቅስቃሴ ከሚጠበቀው በላይ መንግስትን እንዳስጨነቀው በቅርቡ ይፋ የሆነው የአሜሪካ ሚስጥራዊ ሪፖርት አጋለጠ። በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ዶናልድ ያማሞቶ በኖቬምበር 2007 በሚስጢር ያስተላለፉትን ዲፕሎማቲክ መልእክት ከትላንት በስቲያ (ፌብረርዋሪ 16) ይፋ ያወጣው ዊክሊክስ የኦብነግ እንቅስቃሴ ለህልውናየ ከፍተኛ አደጋ ፈጥሯል በሚል የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን አብራርቷል።

  “ምክንያቱ” ይላሉ አምባሳደር ያማሞቶ “ የኢትዮጵያ መንግስት አስኳል የሆነው ህወሐት ከሁለት አስር አመታት በፊት የደርግን ጨካኝ ስርአት ሲጥል የነበረበት ይዞታ ከዛሬው የኦብነግ ይዞታ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ስላገኘው ነው።” አምባሳደሩ አያይዘውም “ጠ/ሚ መለስና የመከላከያ ሚኒስትር ኢታማዠር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ኦብነግን ሰፊ ድጋፍ ከማግኘቱ በፊት ማስወገዱ ወሳኝ ነው።” ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል።

“እንደኛ ግንዛቤ ከሆነ ጠ/ሚ መለስና የኢትዮጵያ መንግስት አመራር አካላት ኦብነግ ለመንግስታቸው ህልውና የሩቅ ጊዜ አደጋ መሆኑን ያምናሉ” የሚሉት አምባሳደር ያማሞቶ በቀድሞዋ ህወሀትና በአሁኑ ኦብነግ መሀል ያለውን ተማስሎ በማጣቀስ ነው።

አምባሳደሩ ይህንን ግምገማ በግላቸው ያቀረቡት ሳይሆን ከራሱ የኢትዮጵያ መንግስት የመነጨ መሆኑን ጠቁመው፦ ከጠ/ሚ መለስ፣ ከጄኔራል ሳሞራና ከሌሎች የህወሐት/ኢህአዴግ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት “ኦብነግ ወደፊት የመንግስት ስጋት ከመሆኑ በፊት አሁኑኑ በወታደራዊ ክንድ መደቆሱ ወሳኝ ነው ብለው እንደሚያምኑ ግልጽ ሆኗል።” በማለት ጽፈዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ በኦብነግ ላይ ያደረባቸውን ፍርሀት የሚገልጸው ግምገማ የተጠቀሰው ኦብነግ በአንድ የቻይና ነዳጅ ፈላጊ ቡድን ላይ ጥቃት ካደረሰና በአጸፋውም የመንግስት ጦር በጭካኔ የተሞላ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከወሰደ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው። የመልሶ ማጥቃቱ እርምጃ ከልክ ያለፈና ፍጹም በጭካኔ የተሞላ እንደነበር የስርአቱ ሁነኛ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካዊው አምባሳደር ሳይቀሩ አምነዋል። 

 

ይሄው የአሜሪካው ሚስጢራዊ መልእክት፤ ጦሩ ከልክ ያለፈ ሀይል መጠቀሙንና ንጹሀን የአካባቢውን ህዝብ በአማጺያኑና በመንግስት ኃይሎች መሀል አጣብቂኝ እንዲገባ እንዳደረገ በተለያዩ የሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ቀርቦ የነበረውን ክስ ትክክለኝነት አረጋግጠዋል። መንግስት ይህንን የሰበአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክስ በጽኑ ያስተባብለው እንደነበር ይታወሳል። 

አምባሳደር ያማሞቶ በቻይና ነዳጅ ፈላጊዎች ላይ በኦብነግ የተወሰደው “በአስደንጋጭ ሁኔታ የተሳካ” ጥቃት ለምን በኢትዮጵያ መሪዎች ላይ ከፍተኛ ፍርሀት እንዳነገሰ ሲገልጹ፦ ‘የመከላከያ ኃይሉ የነዳጅ ፍለጋ ጣቢያውን መከላከልም ሆነ  በአጥቂዎቹ ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ባለበቻሉ እፍረት የተከናነበበት በመሆኑ ነው።” ብለዋል።

 

ይሁንና ከክብር ጥያቄውም በላይ በእጅጉ የሚያሳስባቸው የመንግስታቸው ትልቁ ስኬትና በስልጣን ለመቆታቸውም አይነተኛ ምክንያት በሆነው በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው የከፋ ተጽእኖ ነው። የኦብነግ የጠቃት እርምጃ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የደህንነት ዋስትና እንደሌላቸው ስለሚያመላክት ለመንግስት ‘የኢኮኖሚ እድገት ራዕይ’ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል። ይህም በስልጣናቸው መሰረት ላይ አይነተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል - ባይ ናቸው አምባሳደሩ።

 

በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግስት ኡጋዴን ላይ የወሰደውን በጭካኔ የተሞላ መልሶ ማጥቃት “የውጭ ሰርጎ ገቦችንና አክራሪዎችን” ለማስቆም ነው በሚል የሰጠውን መግለጫ የአሜሪካው አምባሳደር ጥያቄ ውስጥ ከተውታል። “ኦብነግ በኤርትራ መንግስት ይደገፋል የሚለውም ሆነ ሶማሊያዊያን ሰርገው ገብተውበታል የሚለው የመንግስት ክስ አንድም አሳማኝ ማስረጃ ያልቀረበበት ነው” ሲሉ አምባሳደር ያማሞቶ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

 

ኢትዮጵያ ኦብነግ በሽብርተኝነት እንዲመዘገብላት በአሜሪካና በጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት ላይ ግፊት ብታሳድርም እንኳን እስካሁን ከኬንያ በቀር የተቀበላት አላገኘችም። አምባሳደር ያማሞቶም ይህንን ክስ እንደማይቀበሉት በ2007 ዓ. ም ግልጽ ያደረጉ ሲሆን ለኢትዮጵያ መንግስትም ምናልባት አንዳንድ አክራሪዎችን የሚደግፉ ግለሰቦች በውስጡ ሊኖሩ ቢችሉም እንኳን ኦብነግ ሽብርተኛ ድርጅት ነው ብለው እንደማይምኑ አሳውቀዋል። 

 

አምባሳደር ያማሞቶ 'የአቶ መለስ መንግስት የተያያዘው ወታደራዊ ፍጥጫ ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ ስለማይችል ስልቱን እንዲቀይር የአሜሪካ መንግስት ግፊት ሊያደርግ ይገባል' ሲሉ ዋሽንግተንን መክረዋል። ይልቅስ ኋላቀር ለሆነውና በታሪኩም ተገልሎ ለቆየው ለኡጋዴን ክልል የተሻለ ሰብአዊ እርዳታ ነው ሊቀርብለት የሚገባው ሲሉም ይመክራሉ።     

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ