'የአለም ምግብ ድርጅት ታጋቾችን ነጻ አውጥቻለሁ' ኦብነግ

Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. June 2, 2011)፦ በኦጋዴን ክልል የትጥቅ ትግል የሚያካሂደው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር በቅርቡ ባደረገው ከፍተኛ የጥቃት እርምጃ ጂጂጋ አካባቢ የሚገኘውን የጋላሽ ከተማን ተቆጣጥሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ነጻ ማውጣቱንና ብዛት ያላቸው የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን ገልጿል። 

 

እንደ ኦብነግ መግለጫ ከሆነ ከእስረኞቹ መሀል ከሶስት ሳምንት በላይ የደረሱበት ሳይታወቅ የቆዩት ሁለት የተባበሩት መንግስታት የአለም ምግብ ድርጅት ሰራተኞች ይገኙበታል። ባለፈው ሜይ 23 ቀን በአለም የምግብ ድርጅት ሰራተኞች ላይ በደረሰው ጥቃት ሹፌሩ ሲገደል ሁለት ሰራተኞች ደግሞ የደረሱበት ሳይታወቅ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን የግድያውንም ሆነ የአፈናውን እርምጃ ያካሄዱት የኢህአዴግ ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ የኦብነግ ቃል አቀባይ ይፋ አድርገዋል።

 

ለሾፌሩ ሞት ምክንያት የሆነው 'የመንግስት ወታደሮች በአካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያካሄዱትን ጭፍጨፋ ለማየት የቻለ ምስክር በመሆኑ ነው' የሚለው ኦብነግ ሁለቱን ነጻ ያወጣቸውን ሰራተኞችም የአለም የምግብ ድርጅት እንዲረከበው ጠይቋል።

 

በመንግስት ወታደሮች እንግልት ደርሶባቸዋል የሚላቸው ሁለቱ የአለም ምግብ ድርጅት ሰራተኞች ደህንነታቸው በሚጠበቅበት ስፍራ ናቸው የሚለው ኦብነግ ይሁንና ታሳሪዎቹ ሙሉ ነጻነታቸውን ሲያገኙ በመንግስት ኃይሎች የደረሰባቸውን በደል ያጋልጣሉ የሚል ስጋት ያደረበት የኢትዮጵያ መንግስት ርክክቡን ለማደናቀፍ በተዋጊ ሄሊኮብተሮች የታጀበ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍቶብኛል ሲል አማሯል።

 

ለረጅም ዘመናት በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ የቆየው ኦብነግ ለኢህአዴግ አስተዳደር የራስ ምታት ሆኖ መቆየቱ ሲታወቅ በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ያማማቶ ለስቴት ዲፓርትመንት ባስተላለፉት ሚስጥራዊ ሪፖርት ላይ ኦብነግ የኢህአዴግን አስተዳደር ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነው የከተተው ማለታቸውን ከወራት በፊት ይፋ በሆነው ዊኪሊክስ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል። ይህንኑ ስጋት ለማርገብ ሲል መንግስት ከኦብነግ ወጥቻለሁ ከሚል አንድ አንጃ ጋር ባለፈው ጥቅምት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት በመፈራረም 402 እስረኞችን በጥር ወር ነጻ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም ዋናው ኦብነግ ከኢህአዴግ ጋር በትጥቅ ትግል ከመታገል ውጭ ለድርድር የሚያበቃ መሰረት የለም በሚል አቋሙ ጸንቶ ትግሉን እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

 

ክልሉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመገናኘት ሰፋ ያለ የመገናኛ መስመር ያለው መሆኑ አማጺያኑ ሃይል እንደልቡ ለመንቀሳቀስ አስችሎታል የሚሉ ታዛቢዎች በተለይም በቻይናው ነዳጅ አውጭ ሰራተኞች ላይ የተሳካ ጥቃት ካደረሰ ወዲህ ኦብነግ የጥቃት አድማሱን ሳያሰፋ እንዳልቀረ ግምታቸውን ያስደምታጣሉ።

 

በቻይና የነዳጅ ፈላጊ ኩባንያ ሰራተኞች ላይ የሞትና የውድመት አደጋ ካደረሰ በኋላ ፔትሮኖስ የተባለው የነዳጅ ፈላጊ ድርጅት 80ሚሊዮን ብር የከፈለበትን ይዞታውን ለኢትዮጵያ መንግስት አስረክቦ የወጣበት ዋንኛ ምክንያት በአማጺው ኃይል ስጋት መሆኑ ብዙዎችን አስማሚ ክስተት ነው ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

 

በኦጋዴን የጋዝ መሬቶች 9300 ኪሎ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆኑ ሰሞኑን ለተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ለጨረታ መቅረባቸውን ቅርበት ካላቸው የዜና ምንጮች ለመረዳት ተችሏል። ፔትሮኖስ የተባለው ድርጅት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በጋምቤላ ክልልና በ1997 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በኦጋዴን የተለያዩ ቦታዎች የነዳጅ ፍለጋ ስራ ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም እስከ አሁን ይፋ ባላደረገው ምክንያት አካባቢውን ለቆ ወጥቷል።

 

ይሁንና በክልሉ የሚገኙ የነዳጅ ይዞታ ናቸው የተባሉ መሬቶችን የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ለውጭ ድርጅቶች ለጨረታ አቅርቧል። አዳዲስ የነዳጅ ኩባንያዎች ምን መተማመኛ አግኝተው በጨረታው እንደሚካፈሉ ባይታወቅም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ባቀረበው የጨረታ ማስታወቂያ መሰረት ሰባት ነዳጅ ፈላጊ ኩባንያዎች ለጨረታው መቅረባቸውን ሰሞኑን እንዳስታወቀ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው የዜና አውታር ዘግቧል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ