Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 3 ቀን 2003 ዓ.ም. June 10, 2011)፦ በተደጋጋሚ በሚደርስበት የስርጭት ማወኪያ ሞገድ ስርጭቱን አቋርጦ የነበረው የኢሳት የቴሌቪዥን አገልግሎት ኢትዮጵያ መታየት መጀመሩ ይፋ ሆነ። 

 

ኢሳት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሞገድ እወካ ችግሮች በተደጋጋሚ ቢያጋጥሙትም መፍትሄ ሊገኝባቸው የሚችሉበትን ማንኛቸውንም መንገዶች ተጠቅሞ አገልግሎቱን ለመቀጠል ተመልካች የሆነው ህዝብና በተለይ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ያለውን ትብብር አመስግኖ፤ በተለይ ስራውን አጠናክረሮ በKU ባንድ አንድ ተጨማሪ ማስተላለፊያ ጣቢያ ለመክፈት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ከመሆኑም በላይ በተለየያዩ ቦታዎችም ጣቢያዎችን በመክፈት ስርጭቱን እንደሚቀጥል ለመረዳት ተችሏል።

 

ኢሳት በተደጋጋሚ የስርጭት ማወኪያ ሞገድ ሲለቀቅበት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በድረ ገጹ አማካኝነት ስርጭቱን የሚያስተላልፍ መሆኑ ይታወቃል።

 

ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፈው የቴሌቭዥን ቀጥታ ስርጭቱ በተደጋጋሚ የሚታወከው ገዥው መንግሥት በውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በሚከፍላቸው የቻይና ቅጥረኞችን በማሰማራት ነው ሲል ኢሳት በመግለጫው አስታውቋል። ኢሳት ያወጣውን ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች አስፍረነዋል።

 

ኢሳት ESATየኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን

ሰኔ 3፣ 2003 ዓ.ም.

የኢሳትን ወደ ፕሮግራም ሥርጭት መመልስ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ፣

ከሁለት ወር በላይ በደረሰበት ከፍተኛ የዓየር ሞገድ የፕሮግራሙን ሥርጭቅ አቁሞ የነበረው ኢሳት በሰኔ 2፣ 2003 ዓም ወደ መደበኛ ሥርጭቱ መመለሱን ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ በታላቅ ደስታ ነው። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ማንም ሊከለክልህና ሊገድብብህ ሥልጣን የሌለውን እውነተኛ መረጃ የማግኘት ተፈጥሯዊ መብትህን ለማፈን እና እነርሱ የፈለገውን የውሸት ትርኪ ምርኪ ካልሆነ በቀር፣ ሌላ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳታገኝ፣ በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ቀን ከለሊት በደሀ ህዝብ ሥም ለምኖ ባመጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሚከፈላቸው የቻይና ቅጥረኞችን በማሰማራት ኢሳትን በተደጋጋሚ ለማፈን ተንቀሳቅሷል። ይህም በመሆኑ በተለያዩ ጊዚያት ሥርጭታችንን ለማቋረጥ ተገደናል።

ይህ ሁኔታ በተለይ በሀገር ውስጥ ያለውን ወገናችንን ምን ያህል እንደሚያሳስዝነው በተለያዩ መንገዶች የሚደርሱን መልዕክቶች በግልጽ ያስረዳሉ። በኢሳት አካባቢ ያለን ወገኖች አንዳንዶቹን መልዕክቶች እንባ እየተናነቀን ነው የምንሰማቸው። የነጻነት የሲቃ ድረሱልን ጥሪዎች፣ እባካችሁን ቀን አታጨልብን የሚሉ ልብ የሚሰብሩ መማጸኖች፣ የሰማ ህሊናችን የሚያስፈልገውን መስዕዎትነት ከፍለን እየወረድንም እየወጣንም በምንም የማንተወው ጉዳያችን እንዲሆን አድርጎታል።

ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ይህ አስከፊ አፈና በምንም ማሸነፍ የለበትም በሚል ከፍተኛ ስሜት እርዳታ ለሚያደርጉልን በአብዛኛው በውጭ ሀገራት የምትገኙ ወገኖች፣ የፈለገው አፈና ቢካሄድብንም፣ የፈለገው ሴራ ቢሴርብንም፣ የፈቀደው ደንቃራ ቢደረግብንም፣ እውነተኛ እና ሚዛናዊ መረጃ ለወገናችን እየወደቅንም እየተነሳንም ለማቅረብ ዛሬም እንደገና በድጋሚ ቃል እንገባለን።

እንዲያውም በቅርብ ጊዜ በKU ባንድ ተጭማሪ ማስተላለፊያ ጣቢያ ለመክፈት ያለንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻውን ዝግጅት እያጠናቀቅን መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን። ከዚህ በተጨማሪ ለወደፊቱ በበርካታ ጣቢያዎች ኢሳትን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ የምንችልበትን ዕቅድ አውጥተን መጨረሳችንን ስንገልጽ በታላቅ ደስታ ነው።

 

አዲሱ የስርጭት መረጃ፣

ABS1 Satellite 75 degree East

C Band

Down link : 3.480 GHz Vertical (3480)

Symbol Rate: 1.852 Msps (1852)

FEC : 2/3

ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዓይን እና ጃሮ ነው!!!

የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃ የማግኘት ተፈጥሯዊ መብት አለው!!!

ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን፣

ሰኔ 3 ቀን 2003 ዓ.ም.

www.ethsat.com

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ