ለሱዳን ተቆርሶ ተሰጠ በተባለው መሬት ላይ የአቤቱታ ፊርማ ማሰባሰብ ተጀመረ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. May 3, 2008)፦ "የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት የኢህአዴግ መንግሥት ከኢትዮጵያ መሬት ቆርሶ እንደሰጣቸው ለመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ገለፁ" ከተባለ ወዲህ ጉዳዩ በተለይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ እንደቀሰቀሰ ይታወቃል። ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ 35 ኢትዮጵያውያን "በትክክል የኢትዮጵያ የነበረ መሬት፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መቆየት አለበት" በሚል ርዕስ የአቤቱታ ፊርማ (ፔቲሽን) በኢንተርኔት ማሰባሰብ መጀመራቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ከደረሰው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ከእነዚህ 35 ሰዎች ውስጥ 12ቱ ዶክተሮች፣ 3ቱ ኰሎኔሎች፣ አንድ ፕሮፌሠር እና አንድ ኢንጂንየር እንደሆኑ ታውቋል። ፊርማ አሰባሳቢዎቹ መንግሥት በተለይ ሑመራን አስመልክቶ ከሱዳን ጋር አድርጎታል ስለሚባለው ስምምነት ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን፣ የሲቪል ማኅበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠትና ክትትል በማድረግ የመሬቱ ጉዳይ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትኩረት እንዲስብ እና ቀልብ እንዲገዛ ትልቅ ሚና ይጫወቱ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። (ወደ አቤቱታ ፊርማው ውሰደኝ)