Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. August 01, 2008)፦ በስዊድን የሚገኙና ለእግር ኳስ ውድድር በስቶክሆልም ለመሳተፍ ከተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የመጡ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የተቃውሞ ሠልፍ በትናንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄደ። የተቃውሞ ሠልፉ ዓላማ የኢህአዴግ መንግሥት ከምዕራብ ኢትዮጵያ ቆርሶ ለሱዳን መንግሥት የሰጠውን መሬት በመቃወም ነው።

 

ሠላማዊ ሠልፉን ያዘጋጀው በስዊድን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የድጋፍ ማኅበር ሲሆን፣ የተቃውሞ ሠልፉም የተደረገው በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ነበር።

 

ሠልፈኛው ኢህአዴግ ትምክህተኛ ነው፣ ሀገር ከፋፋይ ነው፤ ስለሆነም የኢትዮጵያን ህዝብ አይወክልም በማለት የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል።

 

በተቃውሞ ሠልፉ ላይ ኢህአዴግ ፓርላማውን ሳያነጋግርና የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይወያይበት የሀገራችንን ድንበር ቆርሶ መስጠቱ የዐረቦችን የረዥም ጊዜ ፍላጎት ለማሟላት የተሠራ የድለላ ሥራ ነው በማለት የድጋፍ ማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ታምራት አዳሙ ገልጿል።

 

በመጨረሻም የድጋፍ ማኅበሩ የኢህአዴግን ብሔራዊ የጥፋት አድራጎቱንና ተቃውሞውን የሚገልጸውን ደብዳቤ በስዊድን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽ/ቤት አስገብቷል። አምባሣደሩም የተቃውሞ ማመልከቻውን በመቀበል ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።

 

የዚሁ ደብዳቤ ግልባጭ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ኒውዮርክ)፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አዲስ አበባ)፣ ለስዊድን ፓርላማ (ስቶክሆልም)፣ ለአውሮጳ ሕብረት (ብራስልስ)፣ እንዲሁም ለልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲደርሳቸው መደረጉን ለመረዳት ችለናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ