[ማሳሰቢያ፦ ቪዲዮውን ሕፃናት አይዩት!]

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ነኀሴ 24 ቀን 2003 ዓ.ም. August 30, 2011)፦ የሊቢያው መሪ ልጅ የሆነው የሃኒባል ጋዳፊ ባለቤት ወ/ሮ ኤሊን በፈላ ውሃ ከአናትዋ ጀምሮ ፊትዋንና መላ ሰውነቷን ያቃጠለቻት የ30 ዓመቷን ኢትዮጵያዊት ወጣት ሸዋዬ ሞላ በትሪፖሊ ሆስፒታል እርዳታ እየተደረገላት መሆኑን ሲኤንኤን ዘገበ። አደጋውን ያደረሱት አልጄሪያ ተሰድደዋል።

 

ወጣትዋ ኢትዮጵያዊት በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በሚገኘው ሆስፒታል የቃጠሎ አደጋ ክፍል ውስጥ ሕክምና እርዳታ እያገኘች መሆኑ ታውቋል።

 

ይህንን አደጋ ያደረችው ወ/ሮ ኤሊን ከነልጆችዋና ከባለቤቷ ጋር እንዲሁም ሌሎች ሦስት የሊቢያው የመሪ የሙአመር ጋዳፊ ልጆች ከነቤተሰቦቻቸው በአሁኑ ሰዓት በጎረቤት ሀገር አልጄሪያ ተጠልለው ይገኛሉ። አባታቸው ሙአመር ጋዳፊ ግን እስካሁን የተሸሸጉበት አልታወቀም።

 

ወጣትዋ ኢትዮጵያዊት ለሊቢያው መሪ የልጅ ልጆች ሞግዚት ሆና ትሠራ ነበር። ይህ አደጋ ከደረሰባት ጊዜ ጀምሮ በሃኒባል ጋዳፊ ቤት ውስጥ ተኝታ የቆየች ሲሆን፣ ጋዳፊን ያሸነፉት ኃይሎች የጋዳፊን ልጅ መኖሪያ ሲቆጣጠሩት ፍራሽ ላይ ተኝታ እንደተገኘች ታውቋል።

 

በርካታ ኢትዮጵያውያን ሥራ እና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እንዲሁም ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲሉ ወደ ሊቢያ የሚሰደዱ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በሊቢያ መንግሥት፣ በወታደሮቹና በፖሊሶቹ እንዲሁም በአሠሪዎቻቸው ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው መቆየቱ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!