ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን በመጨረሻ መንግሥት አመነ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ነኀሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. August 21, 2012)፦ በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግሥት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በ57 ዓመታቸው ማረፋቸውን ዛሬ ጠዋት በመንግሥት መገናኛ ብዙኀኑ አማካኝነት አመነ። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ላለፉት ሁለት ወራት ከመገናኛ ብዙኀን ከመጥፋታቸውም በላይ በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን መታመማቸውን ቀጥሎም ማረፋቸውን ቢዘግቡም፤ አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትም አቶ መለስ በሐኪም በታዘዘ እረፍት ላይ መሆናቸውን ሲገልጹና ሲያስተባብሉ መክረማቸው ይታወሳል።
እንደ መንግሥት መገናኛ ብዙኀኑ አባባል ከሆነ ጠ/ሚ መለስ ያረፉት ትናንት ሌሊት ነው። ብዙኀን ግን ይህንን ”ሐሰተኛ ዜና” ነው ሲሉ ይገልጻሉ። የኢህአዴግን አባላት በተለይም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንና ባለሥልጣናትን ለማረጋጋትና ፓርቲው ወደመከፋፈል እንዳያመራ በሚል የጠቅላይ ሚንስትሩን ማረፍ የፓርቲው ጥቂት አመራሮች ደብቀውት እንደነበር ይታመናል።
በተለይም ኢሳት ቴሌቭዥን ሐምሌ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠ/ሚ ማረፋቸውን ከዘገበ በኋላ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ”ሐሰት” ነው በማለት ሲያስተባብሉ እንደነበር አይዘነጋም።
ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በሒልተን ሆቴል መንግሥት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ በጋዜጠኞች እየተጠበቀ ሲሆን፣ ምናልባትም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምዖን መግለጫውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠ/ሚ መቼ የቀብር ሥነሥርዓታቸው እንደሚፈፀም ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠ/ሚ መለስ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ኢትዮጵያን በብቸኝነትና በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው አምባገነኑን የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ሥርዓት ገርስሶ የእርሳቸውን ጨካኝና አምባገነን ሥርዓት መተካቱ ይታወቃል።
አቶ መለስ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው መሪዎች ውስጥ የንግግር ሥርዓት የሌላቸውና ነውረኛ አባባሎችንና ቃላቶችን ”በተከበረው” ፓርላማ ውስጥ እንኳ ሳይቀር ይሰነዝሩ የነበሩ ”ከእኔ በላይ ማንም የለም” የሚሉ ሥርዓት አልባና አምባገነን መሪ ነበሩ።
አቡነ ጳውሎስ
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባለፈው ሣምንት ሐሙስ ነኀሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. (ኦገስት 16 ቀን 2012 እ.ኤ.አ.) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የቀብር ሥነሥርዓታቸው ተነገ ወዲያ ሐሙስ ነኀሴ 17 ቀን (ኦገስት 23) አራት ኪሎ በሚገኘው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ታውቋል።



