“የሞቱት ከ100 አይበልጡም፣ ጥፋተኞች እየተያዙ ነው» የፌ/ጉ/ሚ/ር ሲራጅ ፊርጌሳ

Ethiopia Zare (ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. June 9, 2008)፦ በምዕራብ ወለጋ በተነሳው ግጭት የሞቱ ሰዎች ብዛት 250 እንደሆነ የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሣ (የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር) ለፓርላማው ገለፁ።

 

ኀሙስ ዕለት ተሰብስቦ በነበረው ፓርላማ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሲራጅ ፊርጌሳ ከአቶ ቡልቻ ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በአካባቢው ግጭት መከሰቱን አምነው፣ ከሁለቱ ክልል መንግሥታት በተገኘው መረጃ መሰረት የሞቱት ሰዎች ከመቶ የማይበልጡ ናቸው ብለዋል። አክለውም በግጭቱ የተሳተፉ የአመራር አባላትና ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ሕግ ፊት እየቀረቡ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

 

ግጭቱ ብዙ ሰዎችን ከቀያቸው ያፈናቀለና ብዙ ቤቶች በቃጠሎ እንደወደሙ የገለፁት አቶ ሲራጅ፣ በአሁኑ ጊዜ አካባቢው በፌደራል ፖሊስና፣ በአካባቢው አመራሮች ጥረት ለመረጋጋት ችሏል ብለዋል።

 

በግጭቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉትን የመመለስ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ እና ጊዜው የአዝመራ ወቅት በመሆኑ፣ በቶሎ ወደ እርሻቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ነው እንደ አቶ ሲራጅ ገለፃ። ለተመላሾች የመጠለያ እና የሕክምና ችግር እንዳይከሰት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ በሁለቱም በኩል የተዘረፉ ንብረቶች በአካባቢው ህዝብ ትብብር እየተለዩ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል አቶ ሲራጅ።

 

በአካባቢው ግጭት መነሳት ከጀመረ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ ይህን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት እንዲቻል ከፌዴራልና ከሁለቱ ክልል መንግሥታት የተውጣጣ ኮሚቴ ጥረት በማድረግ ላይ እያለ ነው የዘንድሮ ግጭት የተከሰተው። የአሁኑ ግጭት መጠን ከዛሬ ዓመቱ ያየለና ስፋት ያለው መሆኑን የተገነዘቡት የክልሉ አመራሮች፣ የፌደራል መንግሥት እንዲረዳቸው ጠይቀው ጣልቃ በመግባት አካባቢው ሊረጋጋ መቻሉን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

 

እንደ አቶ ሲራጅ ገለፃ በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የአካባቢው አመራሮችና ታጣቂዎች በህዝብ ጥቆማ እየተያዙ ሕግ ፊት እየቀረቡ ነው። እስካሁን ከሁለቱም ወገን ከ70 በላይ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ችግሩን ለዘለቄታ መፍታት እንዲቻል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ገለልተኛ የልዑካን ቡድን አቋቁሞ ወደ አካባቢው ለመላክ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በማግስቱ ዓርብ ግንቦት 29 ቀን ወደ ቦታው ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

 

አቶ ቡልቻ በበኩላቸው ሚኒስትሩ ያቀረቡት መረጃ ከአካባቢው ከሚደርሳቸው መረጃ በጣም የተራራቀና የችግሩን ጥልቀት ያላገናዘበ ነው ብለዋል። እንደ አቶ ቡልቻ ገለፃ በግጭቱ ምክንያት የሞቱት ሰዎች 250 ሲሆኑ፣ ሁሉም የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው። መንግሥት 80 ብሎ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ቡልቻ አሁን መቶ አድርሶታል፣ በግጭቱም ሁለቱ ወገኖች የተጋጩ በማስመሰል ነው የሚቀርበው፤ ነገር ግን ጥቃቱን ያደረሱት የቤንሻጉል ክልል ነዋሪዎች ናቸው፣ ተኩስ የከፈቱትም በድንገት ሲሆን፣ ከእነሱ ወገን ተጐዳ የሚባል መረጃ የለም ብለዋል።

 

ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ትጥቅ ያስፈታው ደጋማውን ክልል ብቻ ነው የሚሉት አቶ ቡልቻ፤ በቤንሻንገል የሚኖሩ ሰዎች ትጥቅ ያልፈቱ በመሆኑ ጉዳቱን ማድረስ ችለዋል። ከኦሮሞ ወገን አንድም ጥይት የተኮሰ ሰው የለም የሚሉት አቶ ቡልቻ፤ ኦሮሞዎቹ ለዓመታት የያዙትን መሬት ልቀቁ በመባላቸውና አንለቅም በማለታቸው ምክንያት ድንገት በተፈጠረ ጥቃት ነው እልቂቱ የደረሰው።

 

ችግሩ በፍርድ ቤትና በፖሊስ ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ቡልቻ ጉዳዩ የህዝቦች አብሮ መኖርና ሠላምን የሚመለከት በመሆኑ ፓርላማው አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ፣ የደረሰውን ጉዳት ምን ማድረግ እንደሚገባ አጥንቶ፣ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ልዑክ ወደ አካባቢው መላክ ይኖርበታል ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ