የሎንዶኑ ህዝባዊ ውይይትና ተያያዥ ዜናዎች ዝርዝር ዘገባ
የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 7 ንቅናቄ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮጳ ከህዝብ ጋር ይወያያል
Ethiopia Zare (ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. June 9, 2008)፦ ትናንት በእንግሊዝ ዋና ከተማ ሎንዶን ላይ በእንግሊዝ የቅንጅት ድጋፍ ኮሚቴ አዘጋጅነት የተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ከተጠበቀው በላይ በርካታ ታዳሚ በመገኘቱ ሠፋ ወዳለ አዳራሽ የተዛውሮ፣ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ጥቂት ግለሰቦች ለመቃወም ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም እንዳልተሳካላቸው ለመረዳት ተችሏል።
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሰኔ 1997 ምርጫውን ተከትሎ ያደረሰውን ጭፍጨፋ ለመዘከር ታስቦ በተዘጋጀው በዚሁ ህዝባዊ ስብሰባ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች እንደተገኙ ለመረዳት ችለናል። ውይይቱ የተጀመረው በግፍ ለተገደሉት ወገኖች የአንድ ደቂቃ የኅሊና ፀሎት በማድረግ ነበር።
በዚህ ውይይት ላይ ተጋባዥ የነበሩት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ሲሆኑ፣ ሁለቱም በቅደም ተከተል ንግግር አድርገዋል። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “ታማኝነትና ፖለቲካ በኢትዮጵያ፤ ታማኝነት ለማን? ታማኝነት ለምን?” በሚል ርዕስ ንግግር አድርገዋል።
ከዶ/ር ብርሃኑ ንግግር በኋላ ተወያዩ ዕረፍት ያደረገ ሲሆን፣ ከዕረፍት መልስ ሁለቱ ተጋባዥ እንግዶች ከተሰብሳቢው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ከተሰብሳቢዎች በርካታ ጥያቄዎች ለመድረኩ የቀረቡ ሲሆን፣
ከተሰብሳቢዎች አንዱ “በሚቀጥሉት አምስት፣ ስድስት ዓመታት ምን እንጠብቅ?” ብለው ላቀረቡት ጥያቄ ዶ/ር ብርሃኑ ሲመልሱ፤ “… በእኔ እምነት አምስት ዓመት በጣም ረዥም ጊዜ ነው። ኢህአዴግ ከአሁን በኋላ አምስት ዓመት ከቆየ፤ በእኛ ድክመት እንጂ በእሱ ጥንካሬ አይደለም። የምሬን ነው የምላችሁ! እኛ ደካሞች ካልሆንን በቀር፣ ይሄንን በሁሉም መልኩ የተወጠረ መንግሥት፣ ገፍተን ጥለን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን፣ ለአንዴና ለሁሌም አምባገነንነት በዚያች ሀገር የሚያበቃበትን ሁኔታ መፍጠር ካቃተን፤ ችግሩ ያለው ኢህአዴግ ጋር አይደለም። ችግሩ ያለው እኛ ጋር ነው። እሱን ደግሞ መፍቀድ የለብንም። …” ብለዋል።
አክለውም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር እየታገሉ ያሉ ወገኖችና የፖለቲካ ልዩነታችንን በምርጫ የምንፈታባት ኢትዮጵያ የምትባል አንድ ሀገር አለች ብለው የሚያምኑ ኃይሎች የትግል መንገዳቸውን በግልጽ ከቆረጡ፣ እነኝህ ኃይሎች በመሃከላቸው ያለውን ልዩነት ወደፊት በሚደረግ ምርጫ ለመፍታት ከተዘጋጁ፣ ኢህአዴግ አምስት ዓመት የሚቆይበት ምንም ምክንያት እንደማይታያቸው ገልጸዋል።
በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ ከተሰብሳቢዎች በርካታ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል። ጥያቄዎቹ ከቅንጅት መመስረት ጀምሮ እስከ አሁን ባሉት ጉዳዮች ላይ ተመስርተው የቀረቡ ናቸው። ጠቅላላ ውይይቱ ወደ አምስት ሰዓት የፈጀ ሲሆን፣ ውይይቱ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱንም ለመረዳት ችለናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህንን ውይይት ለመቃወም የሞከሩ ጥቂት ግለሰቦች እንደነበሩ የተረዳን ሲሆን፣ ሙከራቸው ያልተሳካ እንደነበር ለመረዳት ችለናል። ይህንን አስመልክቶ አንዳንድ ወገኖችን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን አነጋግረናል።
አንድ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ “አባዱላ ገመዳ እና አዲሱ ለገሠ ሎንዶን ባደረጉት ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ምንም አይነት ተቃውሞ ያላሰሙ ጥቂት ግለሰቦች ይሄንን ውይይት ለመቃወም መሞከራቸው አስቂኝ ሆኖብኛል” ብለዋል።
አብዛኞቹ ያነጋገርናቸው ወገኖች በተለይ ተቃዋሚዎች በተቃዋሚች ላይ መነሳታቸው አግባብነት የሌለውና፤ በጋራ ሊቃወሙት የሚችሉት ኃይል እያለ እርስ በእርስ መፏከታቸው አሳፋሪ መሆኑን ገልፀዋል። ለሁሉም ወገኖች ክፍት በሆነ እንዲህ ባለ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ገብቶ በውይይት ሰዓት የሚቃወሙትን ወገን ሃሳብ በሠለጠነ መንገድ በጥያቄ ማፋጠጥና ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ ሲቻል፤ እንዲህ ያለው በግለሰቦች ላይ ባለ የግል ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ አካሄድ በብቸኝነት ሊጠቅም የሚችለው ገዥው ፓርቲን ብቻ መሆኑን እነኚሁ ያነጋገርናቸው ወገኖች ይስማሙበታል።
በእንግሊዝ ሎንዶን ከተካሄደው የሰኔ ዕልቂቱ መዘከሪያ ህዝባዊ ውይይት በተጨማሪ፣ በትናንትናው ዕለት በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግቶን ዲ.ሲ. ተመሳሳይ ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዷል። በዋሽንግቶን ዲ.ሲ. የተካሄደው ስብሰባም በአንድ ደቂቃ የኅሊና ፀሎት የተጀመረ ሲሆን፣ አቶ ብርሃነ መዋ እና አርቲስት ደበበ እሸቱ ከተጋባዥ ተናጋሪዎች እንደነበሩ ለመረዳት ችለናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ መስፍን አማን የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 14, 2008) ጀርመን ውስጥ ኑረምበርግ በተሰኘችው ከተማ የ”ግንቦት ሰባት የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ”ን አስመልክቶ ከህዝብ ጋር ውይይት ያደርጋሉ። ይህ የንቅናቄውን ዓላማ እና መንፈስ ለህዝብ ለማስረዳት ከህዝብ ጋር በኑረምበርግ የሚደረገው ውይይት በአውሮጳ የመጀመሪያው እንደሆነ ታውቋል።
በተመሳሳይም የፊታችን እሁድ ሰኔ 8 ቀን በጀርመን ፍራንክፈርትም ሁለቱ የፓርቲው መስራቾች ንቅናቄውን አስመልክተው ከህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ለማውቅ ችለናል። ከዚህም ሌላ በአውሮጳ ከሚገኙ የንቅናቄ ደጋፊዎች እና ከኢትዮጵያውያን ጋር በተከታታይ፤ በኖርዌይ - ኦስሎ፣ በስዊድን - ስቶክሆልም፣ እንዲሁም በእንግሊዝ - ሎንዶን ቀጣይ ውይይቶች እንደሚኖሩ ለመረዳት ችለናል።
ንቅናቄው በአውሮጳ ከህዝብ ጋር የሚያደርገውን ውይይት ሲጨርስ፤ በመቀጠል በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ ከተሞች ከደጋፊዎቹና ከኢትዮጵያውያን ጋር በርካታ ውይይቶችን እንደሚያደርግ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።
የሎንዶኑን ውይይት በድምፅ እና በጽሑፍ ያቀረብነውን ለማድመጥና ለማንበብ የሚከተሉትን ይጫኑ!



