በስዊድን የኢትዮጵያ ስደተኞች ማኅበር አባላት ከጋዜጠኛ ዮሐን ፐርሾን ጋር ተወያዩ

ማትያስ ከተማ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም. October 17, 2012)፦ በኢትዮጵያ እስር ቤት ለአስራ አራት ወራት ያህል በእስር የቆዩት ጋዜጠኛ ዮሐን ፐርሾን እና ጋዜጠኛ ማርቲን ሺቢ ከእስር ተለቀው ወደ ስዊድን ከገቡ በኋላ በተለያየ ጊዜና ቦታ ስዊድን ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛሉ።

ባለፈውም ሀሙስ ኦክቶበር 11, 2012 ዓ.ም. በስዊድን የኢትዮጵያ ስደተኞች ማኅበር ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት፤ ጋዜጠኛ ዮሐን ፐርሾን በሥፍራው ተገኝቶ ፍቃድ ለማግኘት ከሚጠባበቁ ኢትዮጵያውያን ስደተኖች ጋር ለሁለት ሰዓት ያህል ውይይት አድርጓል።
ለተሰብሳቢው ውይይቱን የከፈቱት የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ፋንታሁን አሰፋ ሲሆኑ፣ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ስለውይይቱ ከሰጡት አጭር ገለጻ በኋላ የማኅበሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ግሩም ጌታ ዘላለም መግለጫ እንዲያቀርቡ ጋብዘዋል።
አቶ ግሩም ጌታ በሁለት ከፍለው ባሰሙት መግለጫ ብዙኀንን የማይወክለው የኢትዮጵያ መንግስት ምዕራባውያንን በማታለል የቆየ ከመሆኑም በላይ በ2005 እና 2010 ብሄራዊ ምርጫ ማንነቱ በይፋ የተመሰከረበት መሆኑን አስታውሰው፤ አሁንም በሽብርተኛነት የሃሰት ክስ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና ጋዜጠኞችን እያሰረ በማሰቃየት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የስዊድን የስደተኞት ማኅበር መመስረት ስላስፈለገበት ደግሞ ሲገልጹ፤ ከሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመተባበር ለመስራትና የስደተኛውንም ችግሮች ለሚመለከታቸው ክፍሎች በማሳወቅና መፍትሄ ለማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል።
ከዚህ በኋላ ባለው ሰዓት ውይይቱ ቀጥሎ ከተሰብሳቢውና ከአዘጋጆቹ ለቀረቡት ጥያቄዎች ጋዜጠኛ ዮሐን መልስ ሰጥቷል። ከጥያቄዎቹና ከመልሶቹ መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ መንግስት እስር ቤት ተሰቃይተሃል፣ ክስም ተመስርቶብህ ታስረሃል፣ ለመሆኑ ፍርድ ቤትች ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ መስለው ይታይህ ነበር?
ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈጻሚ አንድ አካል በሆነበትና ሁሉንም መንግስት በሚያዝበት ሃገር እንዴት ፍርድ ቤት ነጻ ሊሆን ይችላል? ፍጹም ነጻ እንዳልሆነ አውቃለሁ።
የሀሰት ክስ በግለሰቦች ላይ ተቀነባብሮ የሚለጠፍባቸውንስ እንዴት ታየዋለህ?
ለዚህ እሩቅ መሄድ የሚገባኝ አይመስለኝም። እኛ ስንያዝ ቆስለን ነበር ያሰብነው፤ መጀመሪያ ወደ ህክምና ጣቢያ ይወስዱናል የሚል ነው። እነሱ ግን ያደረጉት የሃሰቱን ክስ ለማቀነባበር እንዲረዳቸው እስከነ ቁስላችን ትያትር እንድንሰራ ነበር ያደረጉን። ስለዚህ በኛው ላይ የደረሰው እራሱ ለዚህ መረጃ ነው።
እናንተ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቃችሁ ስትገቡ ምን ተማምናችሁ ነው? ምንም አያደርጉንም ብላችሁ አስባችሁ ነበር?
ችግር እንዳለ እናውቃለን ዲሞክራሲም እንደሌለ መረጃ አለን፤ ነገር ግን ከዛ በፊት የያዟቸውን ጋዜጠኞች ካሰሩ በኋላ ጥያቄ ጠይቀው ለቀው ነበር። የኛም ከዚህ ይዘላል ብለን አላሰብንም ነበር።
የናንተ መታሰር አስደስቶኛል። በሌላ በኩል ደግሞ የደረሰባችሁ አሳዝኖኛል። ያስደስተኝ እኛ ስንጮህ ማንም ጆሮውን ከፍቶ ሊሰማን አልፈለገም ነበር፤ ከናንተ እስር በኋላ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ ትኩረት ስቦ ብዙ የዜና ጣቢያውች ሊያወሩት ቻሉ። ይሄን እንዴት ታየዋለህ? ሁኔታውንስ ለማጋለጥ ምን ዝግጅት አላችሁ?
አዎን የተለያዩ መንግስታትና የዜና አውታሮች ሁኔታውን እያውቁ ዝም ብለው ቆይተዋል። ሁለት ቆዳችን የነጣ ስንታሰር ግን ሁሉም አይኑን ከፈተ። አሁን ትኩረት ሰጥተው ለመስማት ዝግጁ ሆነዋል። ስለዚህ ያየነውን ችግር በተለያየ መልክ ለማሳወቅ እንጥራለን።
ለመሆኑ በእስር በቆያችሁበት ጊዜ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን የማየት እድል አጋጥሟችኋል?
የለም አላጋጠመንም። እኛን ከነሱ ጋር አልቀላቀሉንም። ለነገሩ እነሱንም ሆነ ሌሎቹን ጋዜጠኞች ብናገኝም እዚህ ለመናገር ፍቃደኛ አይደለሁም።
በእስር በቆያችሁበት ጊዜ ያለው ችግር ለመገንዘብ በቂ መረጃ ሊኖራችሁ ችሏል። እኛ እዚህ ያለን ፍቃድ የሌለን ስደተኞች ያለውን ችግር ስናስረዳ ሰሚ ልናገኝ አልቻልንም ማስረጃ ለማስመጣትም ችግር አለብን። ይሄንን ለስደተኞች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ለማስረዳት ፈቃደኛ ናችሁ?
ይሄ አሳሳቢ ነገር ነው። እቤቴ እንኳን ሆኜ እዛ በእስር ያሉት ጓደኞቼ ትዝ ሲሉኝ በጣም እጨነቃለሁ። እናንተም ከዚህ ብትሄዱ የሚጠብቃችሁ ከዚህ የሚለይ አይደለም። ሁኔታውን ለስዊድን የኢሚግሬሽን ባለስልጣን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ፓርላማ ጭምር እንዲያውቀው ሌሎች ክፍሎችም እንዲረዱት እናደርጋለን።

ጋዜጠኛ ዮሐን በዚህ መልክ ለነዚህና ለሌሎችም ጥያቂዎች መልስ ሰጥቷል። በመጨረሻም ለእሱና ለጋዜጠኛ ማርቲን ሸቢ ከስደተኛ ማኅበሩ ስጦታ ተበርክቶላቸው በፎቶ መነሳት ስነሥርዓት ውይይቱ ተጠናቋል።




