በድምሩ 1900 እስረኞች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ከእስር ይፈታሉ

ጋዜጠኞች ዮሐን ፐርሾን (በግራ) እና ማርቲን ሺቢ (በቀኝ) Johan Persson (L) and Martin Schibbye (R)Ethiopia Zare (ሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2004 ዓ.ም. September 10, 2012)፦ ላለፉት አስራ አራት ወራት በእስር የቆዩትና በሽብረተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው የ11 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሺቢ እና ዮሐን ፐርሾን ዛሬ ጳጉሜን 5 ቀን ማምሻውን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከ11 ሰዓት በኋላ መፈታታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋገጡ። ከቃሊቲ ወጥተው በቀጥታ ወደ ስዊድን ኤምባሲ መሄዳቸው ታውቋል።

 

ባለፈው ዓመት እ.ኤ.አ. 2011 ጁላይ 1 ቀን ጋዜጠኞቹ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባርን (ኦብነግ) እና በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ሲዘግቡ በወቅቱ ከኦብነግ ጋር ውጊያ የገጠመው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከታጣቂዎቹ ጋር ማርኳቸው እንደነበር ይታወሳል። ጋዜጠኞቹና የኦብነግ ተዋጊዎች ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ኦጋዴን ውስጥ ነበር የተያዙት። በወቅቱ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ጥቂት የኦብነግ ተዋጊዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ጋዜጠኞቹም ቆስለው ነበር።

 

ጋዜጠኞቹ ማርቲን ሺቢ እና ዮሐን ፐርሾን (ፎቶግራፈር) ከተያዙ በኋላ ካለፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት እና በ”ሽብረተኝነት” ክስ ተመስርቶባቸው ነበር። እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 21 ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቶ ሲያበቃ ዲሴምበር 27 ደግሞ የ11 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸው ነበር።

 

ፍርድ ቤቱ ለሰጠው የቅጣት ውሳኔ ይግባኝ ሳይሉ በመቅረት የይቅርታ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በሟቹ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እንደተፈረመበት የተነገረው ይኸው የ”ይቅርታ” ጥያቄያቸው በዛሬው ዕለት ተፈጻሚ ሆኖ ተፈትተዋል። በዛሬው ዕለት አዲሱን የኢትዮጵያ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሁለቱን ጋዜጠኞች ጨምሮ ለ1900 እስረኞች ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑ ታውቋል።

 

ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬ በ”ሽብረተኝነት” በሚል ተከስሰው እስራትና የገንዘብ መቆጮ ተጥሎባቸው በእስር እንደሚገኙ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ