HAPIUNESCO እና ከUNOHCHR ጋር በመተባበር ነገ ጠዋት በረቂቅ አዋጁ ላይ ሴሚናር አዘጋጅቶ ነበር

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. July 1, 2008)፦ ከአምስት ዓመት በፊት ኅዳር 25 1995 ዓ.ም. የተረቀቀውና፣ ጥር 5 ቀን 1995 ዓ.ም. (January 13, 2003) ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበትና አፋኝ መሆኑ ሲነገርለት የነበረው አዲሱ የፕሬስ ሕግ ዛሬ በፓርላማው መጽደቁን ለኢትዮጵያ ዛሬ ከአዲስ አበባ የደረሰው መረጃ ጠቆመ።

 

ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ሲንከባለል የመጣውና በመጨረሻም ባለፈው ሚያዝያ 2000 ዓ.ም. ላይ “የመገናኛ ብዙኀን እና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ” ተብሎ ፓርላማው ተወያይቶበት እንደነበር አይዘነጋም። ይሄንኑ ኢህአዴግ አቅርቦት የነበረውን አዲስ ረቂቅ የፕሬስ ሕግ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉ ተቃዋሚዎች፣ በርካታ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ማኅበራት (ሲፒጄ፣ አይኤፍኤክስ፣ አር.ኤስ.ኤፍ.፣ …)፣ ኢነጋማ (የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማኅበር)፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ … ሁሉም ወገኖች ላለፉት አምስት ዓመታት ከአምስት ወራት ሲቃወሙት፣ አፈኝ ነው ሲሉት፣ ማሻሻያ ይደረግበት ዘንድ ሲጮሁ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።

 

ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. (July 1, 2008) ተሰብስቦ የዋለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማው) ይህንን አፋኝ የፕሬስ ሕግ ብዙም ማሻሻያ ሳያደርግ በማጽደቁ ብቸኛው ተጠቃሚ ኢህአዴግ ብቻ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

 

ነገ ቀኑን ሙሉ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል እስከ ከሰዓት በኋላ ረፋዱ አስር ሰዓት ተኩል ድረስ “በረቂቅ” አዋጁ ላይ ሆርን ኦፍ አፍሪካ ፕሬስ ኢንስቲትዩት (HAPI) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) እና በተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን (UNOHCHR) ጋር በመተባበር በግዮን ሆቴል ለትምህርታዊ ሴሚናር ጥሪ አስተላልፎ ነበር። በዚህ ትምህርታዊ ሴሚናር ላይ ጋዜጠኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙኀን ወገኖች፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ጥሪው ደርሷቸው ሳለ፤ ኢህአዴግ የፕሬስ ሕጉን አንድ ቀን ቀደም ብሎ አጽድቆታል።

 

ነገ ተጠርቶ በነበረው ትምህርታዊ ሴሚናር ላይ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሑፍ ሊያቀርቡ እንደነበር ታውቋል። ሆርን ኦፍ አፍሪካ ፕሬስ ኢንስቲትዩት ሴሚናሩን ያዘጋጀበት ዓላማ በፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ላይ ሁሉንም ወገኖች ለማቀራረብ የነበረ ሲሆን፣ የፕሬስ ሕጉ መጽደቁ ተቋሙ ያሰበውን ዓለማ ከግብ እንዳያደርስ እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ተገምቷል።

 

ኢህአዴግ ምርጫ 97ን ተከትሎ ትልቁን በትር በፕሬሱ ላይ ካሳረፈ ወዲህ በሀገሪቱ እጅግ በጣም ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች (በተለይም የፖለቲካ ጋዜጦች) ናቸው ያሉት።

 

ምርጫ 97ን ተከትሎ 21 ጋዜጠኞችን ከቅንጅት ከፍተኛ መሪዎች ጋር እስር ቤት ከከተተ በኋላ ያልታሰሩት የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች አብዛኞቹ ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸው ይታወሳል። ከእስር ከተፈቱትና በፕሬስ ሥራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ የጠየቁትም መከልከላቸው ይታወቃል።

 

ምርጫ 97ን ተከትሎ የታሰሩት ከተፈቱ ወዲህ ለጥቂት ጋዜጦች ፈቃድ የተሰጠ ቢሆንም፣ ዛሬ የፀደቀው አዲሱ የፕሬስ ሕግ አሁን በገበያ ላይ ያሉትንም ቢሆን እንደማያሰራቸውና እንደሚያፍናቸው ታውቋል። በዚህም ምክንያት አሁን በሀገር ቤት ያሉት ጋዜጦች በተደጋጋሚ ዛሬ የፀደቀውን የፕሬስ ሕግ ሲቃወሙትና ሲተቹት እንደነበር ይታወቃል።

 

የኢህአዴግ መንግሥት በሀገሪቱ ይሠራባቸው የነበሩትን ሕጎች በ”ማሻሻል” ስም እየቀየረ ሕጎቹን ጨቋኝና አፋኝ እያደረገ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ እየገጠመው መሆኑ ይታወቃል። በቅርቡ የብሔራዊ ባንክ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ፣ የፓርቲ ምዝገባ ደንብ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስመልክቶ የወጣው ረቂቅ ሕግ እና ሌሎችም ያፀደቃቸውና ሊያስፀድቃቸው በዝግጅት ላይ የሚገኙትን ሕጎች አስመልክቶ ብዙዎች “ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምባገነንነቱን እያረጋገጠ የሚገኝበት ወቅት ነው” ብለው እንዲደመድሙ አድርጓቸዋል። ብዙዎች እነዚህ ሕጎች ጎጂነታቸው ለሀገር፣ ለህዝብና ለትውልድ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለገዥው ፓርቲ ለኢህአዴግም እንደሆነ ይስማሙበታል።

 

ዛሬ የፀደቀው አዋጅ ቀድሞ ይሠራበት የነበረውን የፕሬስ አዋጅ ቁጥር 34/85 የሆነውን እንደሚሽረው ታውቋል። ዛሬ የፀደቀውን የፕሬስ ሕግ በእጃችን ያልገባ ቢሆንም፣

 

1) ባለፈው ሚያዝያ 2000 ዓ.ም. ላይ “የመገናኛ ብዙኀን እና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ” ተብሎ ፓርላማው ተወያይቶበት የነበረውን ረቂቅ አዋጅ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ!

 

2) ብዙም ማሻሻያ ያልተደረገበትንና ጥር 5 ቀን 1995 ዓ.ም. ይፋ ተደርጎ የነበረውን ረቂቅ የፕሬስ ሕግ ለማንበብ ደግሞ እዚህ ላይ ይጫኑ!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ