ተጠርጣሪው ጓደኛው ነው

Ethiopia Zare (ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. July 2, 2008)፦ ወጣት ደጉ ተስፋዬ ሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ቤተሰቦቹ ለመመለስ ጊዜያዊ የትምህርት ማስረጃውን ይዞ፣ ዕቃውን ሸክፎ መናኸሪያ ከደረሰ በኋላ፤ የሞባይል ስልኩ ጠፍቶበት ስለነበር ስልኩ መገኘቱን የሚገልጽ መልዕክት ደርሶት ወደ ግቢው ሲመለስ ነው ሦስት ቦታ በጩቤ ተወግቶ የተገደለው።

 

ሟች ደጉ የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ሳይለቅ በፊት ነበር ሞባይል ስልኩ የጠፋበት። ሙሉቀን የሚባለውን ጓደኛውን በሞባይሉ ስርቆት ይጠረጥረዋል። ሙሉቀንም በዚህ እጅግ ተናድዶ እንደነበር ጉዳዩን የሚያውቁ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ይናገራሉ።

 

ደጉ በዩኒቨርሲቲው በኢንቫይሮመንታል ሄልዝ ትምህርቱን አጠናቅቆ ከተመረቀ በኋላ ወደ ቤተሰቦቹ ለመጓዝ ወደ መናኸሪያ ያቀናል። መናኸሪያም እንደደረሰ ስልኩ መገኘቱንና ግቢ እንዳለ መልዕክት ሲደርሰው፣ ይዞት የነበረውን ዕቃውን መናኸሪያ ውስጥ ለሚያውቃቸው እንዲጠብቁለት ሰጥቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ግቢው ያቀናል።

 

እግቢው እንደደረሰም ሦስት ጊዜ በጩቤ ተወግቶ ሕይወቱ ታልፋለች። በግድያው በፖሊስ ተጠርጥሮ የተያዘው የገዛ ጓደኛው የሆነው ሙሉቀን መሆኑ ታውቋል።

 

የዓይን ምስክሮች እንደሚሉት ከሆነ፣ ሙሉቀን ደጉን በጩቤ ከወጋው ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከኪሱ የሆነ ነገር በማውጣት እንደበላ ወዲያውኑ ተዝለፍልፎ ይወድቃል። ከዚያም ወደ ሆስፒታል ይወሰዳል። ሆስፒታል ከገባ በኋላ ሕክምና ሲደረግለት ቆይቶ ሲሻለው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

 

የጅማ ዩኒቨርሲቲ እና የኦሮሚያ ፖሊስ በጋራ ሆነው ከሁለት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር የሟች ደጉ ተስፋዬን አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ሸኝተውታል። የደጉ ቤተሰቦችም ከአዲስ አበባ የልጃቸውን አስከሬን ተቀብለው ጎንደር ውስጥ በትውልድ ሥፍራው ጭልጋ የቀብር ሥነሥርዓቱን ፈጽመዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ