Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. July 19, 2008)፦ ባለፈው እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2000 ዓ.ም. የድሬዳዋ ኤፍ.ኤም. ራዲዮ በከተማው ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ አራተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ስቱዲዮው መደበኛ ዝግጅቱን እያስተላለፈ ሳለ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ53 ደቂቃ ላይ ስቱዲዮ ውስጥ የነበሩት የዕለቱ ተረኛ አዘጋጆች መቆጣጠሪያ እየተባለ ከሚጠራው ክፍል ጭስ ሲጨስ በማየታቸው ዝግጅታቸውን አቋርጠው ዘለው ይወጣሉ።

 

ለምለም ተክሌ የተባለች የራዲዮው ቴክኒሽያን ግን እንደሌሎቹ በፍጥነት በሩን ለመክፈት ባለመቻሏ መስታወት ሰብራ ለመውጣት ተገድዳ፣ በመስታወቱ ስብርባሪ ምክንያትም እጇ ተጎድቷል።

 

የድሬዳዋ ኤፍ.ኤም. ራዲዮ የተቋቋመው ከሦስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ በዚህ ቃጠሎ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት እንደወደመበት ታውቋል።

 

ኤጀንሲው የቴሌቪዥንና የራዲዮ ሁለት ስቱዲዮዎች ያሉት ሲሆን፣ ቃጠሎው የተከሰተው በራዲዮ ስቱዲዮ ላይ በመሆኑ እሳቱን ለማጥፋት እስከ ማምሻው 12 ሰዓት ድረስ የተሞከረ ቢሆንም በአብዛኛው የስቱዲዮው ንብረት ተቃጥሏል፣ በፎቁ ግማሽ አካል ላይም ቃጠሎ ደርሶበታል።

 

የድሬ ኤፍ.ኤም በዕለቱ ሥርጭቱ ይቋረጥ እንጂ በማግስቱ የማሠራጫ ትራንስሚተሩ ወደሚገኝበት ከከተማው 3.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጋራዲማ የተባለ ጋራ ላይ በመውጣት ፕሮግራሙን በማስተላለፍ ላይ እንደሚገኝ የድሬዳዋ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ዑስማን መግለጻቸው ታውቋል።

 

ራዲዮው ፕሮግራሞቹን ባሉት መሣሪያዎች እየቀረጸ እንዲሁም የቀጥታ የስልክ ውይይት ሲኖረውና ዜና በቀጥታ ማስተላለፍ ሲፈልግ ጋራ ላይ እየወጣ በመሥራት ላይ እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል።

 

የድሬዳዋ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ከተቋቋመ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ 43 የሚጠጉ ሠራተኞች አሉት። ከቃጠሎው በኋላም ከእነዚህ ሠራተኞች አብዛኞቹ ለፖሊስ ቃላቸውን ቢሰጡም፣ ፖሊስ ለጊዜው ይፋ ባያደርግም ለቃጠሎው መንስዔ ሊሆን ይችላል በሚል የደረሰበት መረጃ በአሌክትሪክ ብልሽት ሳይሆን እንዳልቀረ ነው።

 

ኤጀንሲው ያለበት ሕንፃ ቀደም ሲል የድሬደዋ የንግድ ምክር ቤት ንብረት ሲሆን በኋላም የከንቲባው ጽ/ቤትና የአቅም ግንባታ ቢሮ ሆኖ አገልግሏል። በአሁኑ ሰዓትም ኤጀንሲውና ክልል ምክር ቤቱ በጋራ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይታወቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ